
በመርሳና አካባቢዋ የእስልምና እምነት ተከታዮች በመስጅድ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በመቃወም ሠላማዊ ሠልፍ አካሄዱ፡፡
በሠላማዊ ሠልፉ ፀረ ሠላም ኃይሎች ብሔርንና ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ብጥብጥና ሁከት ለመፍጠር ያደረጉት ተግባር የሚወገዝ መሆኑ ተገልጿል። መንግሥት ወንጀለኞችን ተከታትሎ ለፍርድ እንዲቀርብና ለተቃጠሉ መስጅዶች ካሳ እንዲከፍልም ተጠይቋል፡፡
የመርሳ ከተማ ከንቲባ አቶ በዛብህ ታደሰ በሰልፉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክ “ትናንት ሲያስሩ፣ ሲገርፉ የአካል ጉዳት ሲያደርሱ የነበሩ ኃይሎች ዛሬ ላይ ተሸንፈው ጥግ በመያዝ የሚያደርጉትን ሴራ የሁሉም የእምነት ተከታዮች በንቃት በመጠበቅ መከላከል ይገባቸዋል” ብለዋልሏ፡፡
ፀረ ሠላም ኃይሎች በፖለቲካ ሳይሳካላቸው ሲቀር በብሔርና በሃይማኖት የሚያደርጉትን ብጥብጥና ሁከት በማውገዝ በእምነት መቻቻልንና መከባበርን እንደሚያሥተምሩም ሠልፈኞቹ ገልጸዋል፡፡
የሀገር ሽማግሌዎችና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ አባቶች በሰልፉ ላይ በመገኘት በእምነት ተቋማት ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በመቃወም አውግዘዋል፡፡ ሠላማዊ ሰልፉ ባለ ስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ሰልፉ በሠላም መጠናቀቁን የሀብሩ ወረዳ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ነው፡፡