
ባሕር ዳር: ሐምሌ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላምን ለማፅናት ልማት ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የልማት ሥራ እንዲጠናከር የድርሻውን እንደሚወጣ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አስታውቀዋል። የዕዙ አባላት ለ24 ሰዓት ብረት በማቅለጥ የግንባታ ፌሮን ጨምሮ ብረታብረት የሚያመርተው ራቫል ብረታብረትን እንዲሁም አማራ ፓይፕ ፋብሪካ፣ ሻምበል ዘይት ፋብሪካ፣ አዲሱ የዓባይ ድልድይን እና ልዩ ልዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል። ሠራዊቱ ሀገሪቱ በጦርነት ውስጥ ሆና ያልተቋረጠውን የፕሮጀክት አፈፃፀም መመልከቱ ዋጋ የከፈለለትን ዓላማ የሚያጎላ ስለመሆኑ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች በጉብኝቱ ወቅት ገልጸዋል።
ሰላም ለሁሉም ነገር ቁልፍ ጉዳይ ነው ያሉት የዕዙ ዋና አዛዥ ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ፣ ሰላምን ለማፅናት ኅብረተሰቡን የሚያሳትፉ እና ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች መጠናከር አለባቸው ብለዋል። የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አባላት መሥዋዕትነት የከፈሉለት ሀገር እና ሕዝብን የመጠበቅ እና ትኩረቱን ልማት እና አንድነት ላይ እንዲያደርግ በመሆኑ በተመለከቱት የልማት ሥራ መደሰታቸውንም ገልጸዋል። ለዘላቂ ሰላም እና ልማትም የድርሻቸውን እንደሚወጡ መናገራቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!