የሰው እና የእንሰሳ ሕይወት በየክረምቱ ይቀጥፍ የነበረው የአሻር ወንዝ ድልድይ ግንባታ ተጠናቀቀ።

66

ባሕር ዳር: ሐምሌ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎጃም ዞን በደቡብ አቸፈር ወረዳ የአሻር ወንዝ ድልድይ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል። በሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ አቸፈር ወረዳ የቦደን ሀና ቀበሌ የሚገኘው የአሻር ወንዝ ርዝመቱ 42 ሜትር የሆነ ድልድይ በክልሉ መንግስት በ46 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።

የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሀመድ ያሲን ቢሮው በ2015 በጀት ዓመት “ፕሮጀክት ላንጨረስ አንጀምርም” በሚል ቃል ሌሎችን ፕሮጀክቶችን ትተን በድልድይ ዘርፍ ያለውን ብቻ ወሰደን ብናይ 23 የኮንክሪት እና 21 የተንጠልጣይ ድልድዮችን በማቀድ 43 የሚሆኑትን አጠናቅቀናል ብለዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ የአሻር ድልድይ ነዉ ብለዋል።

የቦድን ሀና ቀበሌ ነዋሪዎችም በበኩላቸው በርካታ የሰው እና የእንሰሳ ሕይወት በየክረምቱ ይቀጠፍ ነበር ። ስለሆነም ከብዙ ጥያቄ በኋላ ምላሽ አግኝተናል እና እኛም የሚጠበቅብንን ድጋፍ እንክብካቤ እያደረግን በአግባቡ ማገልገል የሚገበውን ያህል እድሜ እንዲያገለግል የድርሻችንን እንወጣለን በማለት ሀሳባቸውን በደስታ ገልፀዋል።

እንደ ሰሜን ጎጃም ዞን ኮሙኒኬሽን መረጃ በመድረኩ የርዕሰ መስተዳድሩ ተወካይና የአብክመ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ዳኝነት ፈንታ (ዶ.ር) እና የምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪና የብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ መልካሙ ተሾመ ተገኝተው መልእክት አስተላልፈዋል።

📸 አማራ መንገድ ቢሮ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሮም ለአትሌት አበበ ቢቂላ መታሰቢያ ምስለ ቅርጽ አኖሩ
Next articleከሞላሌ አዳባይ ያለው የመንገድ ፕሮጀክት የሸዋ የማዕድን ፣ የግብርና እንዲሁም የቱሪዝም መዳረሻ ማዕከል መኾኑ ተገለጸ።