
ባሕር ዳር: ሐምሌ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ በመካነሰላም ግቢ በመደበኛው እና በማታው መርሐ ግብር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው ለአራተኛ ጊዜ ነው ተማሪዎችን ያስመረቀው። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ፕሮፌሰር ከፍያለው አለማየሁ መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ሀገርን የሚረከብ መልካም ዜጋ የማፍራት ኀላፊነቱን በትጋት እየተወጣ ያለ ዩኒቨርሲቲ መኾኑን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው የተጣለበትን ኀላፊነት እየተወጣ ለመኾኑ የሀገር አቀፍ የመውጫ ፈተና ተፈትነው ለምረቃ የበቁት ተማሪዎች ሁነኛ ማሳያ ናቸው ብለዋል።
“ሀገራችሁ ኢትዮጵያ ፍቅርን፣ መተባበርንና መተሳሰብን በምትሻበት እንዲሁም ለሀገር መቆም ለእውነት መታገል የህልውና ጉዳይ በኾነበት ወቅት የተመረቃችሁ በመኾኑ ልትኮሩ ይገባል” ብለዋል። ተመራቂዎች ወደ ሥራ ሲሰማሩ ከወገናቸው ጎን በመቆም ለሀገራችው ሰላም ለወገናቸው ዕድገት የበኩላቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
“የሀገርን ጥሪ ተቀብሎ ለማስተናገድ ሁለንተናዊ ብቃት እና በሳል አስተሳሰብ አስፈላጊ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ከፍያለው በዩኒቨርሲቲው ባገኛችሁት ዕውቀት ብቻ ሳይኾን የሀገር ፍቅር ስሜት እና ትርጉም ያለው ሕይወት የመምራት ክህሎትን ፤ ከምትኖሩበት ማኅበረሰብ ያለመታከት በመማር መኾኑን ልብ ልትሉ ይገባል ብለዋል።
“ሳይማር ያስተማራችሁ ሕዝብ የተሻለ ሕይዎት እንዲኖር በዩኒቨርሲቲው ያገኛችሁትን ውጤት በተግባር ለውጣችሁ የሚታይ ለውጥ ማስመዝገብ ይኖርባችዃል ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ።
ማወቅ እና መመኘት ብቻውን የምንጠብቀውን ውጤት አያመጣም ያሉት ፕሮፌሰሩ የሰው ልጅ ሀሳብ እና ዕውቀት መነሻ ይኾናል እንጅ ብቻውን ውጤት አያመጣም፤ ሀሳባችሁን በተግባር መለወጥ ይጠበቅባችኋል ነው ያሉት። ለዚህ ነው እስካሁን ሀገራችንን ከተሻሉ ሀገራት ተርታ ማሰለፍ ያልቻልነው እና የፈለግነውን የሀገር ፍቅር ማምጣት ያልቻልነው ሲሉ አብራርተዋል።
እናንተ የተማራችሁትን በተግባር በመተርጎም የተጣለባችሁን የትውልድ አደራ በብቃት ልትወጡ ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!