ግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴን የሚዘክር ሀውልት በአዲስ አበባ አማካይ ቦታ ላይ እንዲገነባ ተጠየቀ።

73

👉የግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ 131ኛ ዓመት የልደት በዓል በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው።

አዲስ አበባ: ሐምሌ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ፋውንዴሽን ያዘጋጀው የልደት ዝከረ በዓል ነው እየተከበረ የሚገኘው።

ሐምሌ 16/1884 ዓ.ም የተወለዱት ግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ 1923 ዓ.ም በንጉሠ ነገሥትነት ኢትዮጵያን መምራት መጀመራቸው ይታወቃል።

ግርማዊነታቸው በዘመናቸው ካከናዎኗቸው ታላላቅ ሥራዎች መካከል በኢትዮጵያ፦

👉 ዘመናዊ ትምሕርትና ሥነ ጥበብ እንዲስፋፋ።
👉ከኋላቀር አስተሳሰብና ባሕል ወደዘመናዊ እና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ማኅበራዊ መዋቅርና አሥተዳደር ሽግግር እንዲኖር አስችለዋል።
👉 የኢትዮጵያ ነፃነትና ክብር እንዲሁም ሰላም ወዳድነት በዓለም መድረክ ጎልቶ እንዲታይ ያደረጉ በመኾናቸው በታሪክ መዝገብ ላይ ጉልህ ስፍራም ይሰጣቸዋል።
በአፍሪካ ደረጃ ደግሞ፦
👉 የአፍሪካ ወንድሞችና እህቶች ከቅኝ ተገዢነት ተላቅቀው በነፃነት እንዲኖሩ
👉ኅብረት እንዲመሠርቱና በሰላም የራሳቸውን ሀገር በራሳቸው እንዲመሩ ተጋድሎ አድርገዋል።

በዓለማቀፍ ደረጃም፦

ዓለም በሁለት ጎራ ተከፍላ ምሥራቃዊና ምዕራባዊ እሳቤ በሚል ችግር ውስጥ በነበረችበት ወቅት ለዓለም ሰላም የጣሩና ከማንኛውም የዓለም መንግሥታት ወዳጅነት እና ትብብር መፍጠር የቻሉ መሪ ነበሩ።

የግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ፋውንዴሽን የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ አይዳ ኃይለማርያም ባደረጉት ንግግር ፤ ፋውንዴሽኑ ከትምህርት ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነትና ስኮላርሺፕ መምሪያ ጋር ባለው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት በጦርነት ከተጎዱ አካባቢዎች በሚገኙ 10 ዩኒቨርሲቲዎች 60 የኢኮኖሚ አቅም የሌላቸው ተማሪዎችን ተቀብለው እያስተማሩ መሆኑን ገልጸዋል።

👉 የቦርድ ሰብሳቢዋ የፋውንዴሽኑ ወዳጆች በአሜሪካ ባደረጉት ድጋፍ በዘንድሮው ዓመት ብቻ 50 ተማሪዎችን እየደገፈ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
👉ግርማዊነታቸው ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ያስከበሩ የአፍሪካ አባት ናቸውና ለክብራቸውና ታሪካቸው፤ የትውልድ መዘከሪያ በአማካይ ቦታ ላይ ሀውልት እንዲቆም የጠየቁት ሰብሳቢዋ ይህንኑ ጥያቄ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በደብዳቤ ተጠይቆ መልስ እየተጠበቀ መኾኑን ተናግረዋል።
👉 የፋውንዴሽኑ ዋነኛ ማነቆ የኾነውን የጽሕፈት ቤት ችግር ለመፍታት እንዲቻል የደርግ መንግሥት ከቀድሞው ዐፄ ኃይለሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅት ከወረሳቸው ንብረቶችና ሕንፃዎች መካከል እንዲመለስላቸው ተጠይቋል።
👉”የአፍሪካ ጥናትና የቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ አበርክቶ” በሚል የአፍሪካ ታሪክ ተመራማሪው አየለ በኸሪ (ዶ.ር)
👉”የቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ የዲፕሎማሲ ስኬት በአፍሪካ አህጉርና በዓለም አቀፍ” በኢኮኖሚ ምሁሩ ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ.ር) እና
👉 “የቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ የአመራር ውርስና ዶክተር መላኩ በያን” በሚል ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንዲሳካ አስተዋጽዖ ላደረገው የአፍሪካ ሕብረት ዕውቅና ተሰጠ።
Next articleየ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ ጡት የሚያጠቡ ሴት ተፈታኞች ሞግዚት ይዘው እንዲገቡ ተፈቀደ።