
ባሕር ዳር: ሐምሌ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዘመን ተሻጋሪ እውነት፣ በአዝማናት መካከል የማይዋዥቅ ሃቅ፣ በተፅዕኖ የማይደበዝዝ ሀገራዊ ማንነት እና እልፍ የታሪክ ምስክሮችን አቅፈውና ሸክፈው ከያዙ ቀደምት ሀገራዊ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት፡፡ ወርቅ አንጥራ ረቂቅ መልዕክት፣ ብራና ፍቃ ጠሊቅ ዕውቀት፣ ዓለት ፈልፍላ እልፍ አብያተ ክርስቲያናት፣ ደን ተክላ ብዝሃ ሕይዎት እና ሐይቅ ላይ ጸንታ ዘላለማዊነት የሚስተዋልባት ቤተ ክርስቲያኗ ከውስጥም ከውጭም ለሚነሱ የማንነት ጥያቄዎች በቂ ምላሾች አሏት፡፡
ቤተ ክርስቲያኗ ዘመን በተቆጠረበት እና የሰው ልጅ ምድር ላይ በኖረበት ጊዜ ሁሉ ያከማቸቻቸው ቅርሳቅርስ፣ ጥበብ፣ እውቀት እና ብልሃት ለአሁናዊዎቹ የሀገሪቱ ፈተናዎች ምላሽ ሲሆኑ ተስተውሏል፡፡
በሕገ ልቦና፣ በሕገ ኦሪት እና በሕገ ወንጌል ያለፈችው ቤተ ክርስቲያኗ ወይፈኑን አቅንታ እና አብያውን አስልታ ለቤተ መንግሥት ያበቃች ባለውለታም ተደርጋ ትታወሳለች፡፡ በኢትዮጵያ ጥንታዊ እና ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ የቤተ ክርስቲያኗ ደርሻ እጅግ ጉልህ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡
ኢትዮጵያ በተፈተነችበት ወቅት ሁሉ ውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተናዎችን ያሳለፈችው የኦትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ድርሳናትን ከትባ፣ ፊደል ቀርጻ፣ ስዕል አስማምታ እና ሰው አፍርታ ትውልድ እንዲቀጥል አድርጋለች፡፡ ይኽ እውነት ዛሬም ድረስ ነፍስ ዘርቶ እና ስጋ ነስቶ የሚገኝ ሃቅ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ሰማይ ስር አዘውትረው ለሚከሰቱ ውስጣዊ ልዩነቶች እና ውጫዊ ተፅዕኖዎች በቂ ምላሽ በአጽደ ከተከበበችው ቀደምት ተቋም ውስጥ ይፈልቃል፡፡
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ወልቃይት ወረዳ ኩሊታ ብላምባ ቅርሽ ቀበሌ ደብረ ገነት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አጽድ ሥር ተገኝተናል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ አያሌ ዘመናትን እንዳስቆጠረ ዙሪያውን አይቶ መገንዘብ ይቻላል፡፡ እድሜ ያስቆጠሩት ታላላቅ ሀገር በቀል ዛፎች ለቤተ ክርስቲያኗ የተለየ ግርማ ሞገስ አላብሰዋታል፡፡ የአዕዋፋቱ ህብረ ዝማሬ ከዓለማዊነት ወደ መንፈሳዊነት ያሸጋግራል፡፡
የደብሩ አካባቢ ከባድ ጸጥታ የተለየ ፍርሃትን ይፈጥራል፡፡ የቤተ ክርስቲያኑን ዙሪያ ጥቅጥቅ ደን መጠጊያቸው ያደረጉት የዱር እንስሳት እንቅስቃሴ ቅጠል ኮሽ ባለ ቁጥር ከሩቅ ሳይቀር ይሰማል፡፡ በዚህ አካባቢ መገኘት በራሱ የተለየ ስሜትን ይፈጥራል፡፡
በደኑ ውስጥ ባለች ቀጭን መንገድ ውስጥ ትንሽ እንደተጓዝን ያገኘነው የመካነ መቃብር ቦታ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እድሞ ስር ስለመቃረባችን ፍንጭ ይሰጣል፡፡ ጸጥታ እና እርጋታ የበዛበት የቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ ከመካነ መቃብሩ ጋር ተደምሮ የተለየ የፍርሃት ድባብን ይፈጥራል፡፡ ደማቅ ቀለም የተቀባው የቤተ ክርስቲያኑ ህንጻ ከእድሞው ቀድሞ ተገለጠልን፡፡ ቀድመን ቀጠሮ ስላስያዝን የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ እና ሌሎች ካህናት እንደሚጠብቁን ተነግሮናልና ከቤተ ክርስቲያኑ እድሞ ዘልቀን ከገባንም በኋላ በአካባቢው ሰው እየፈለግን ነው፡፡
አንድ የተለየ ግርማ ያለው ድምጽ ከቤተ ክርስቲያኑ ህንጻ አካባቢ ስንሰማ ጆሯችንንም ዐይናችንንም ወደዚያው ወረወርነው፡፡ ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ሁለት ቀሳውስት ከቤተ ክርስቲያኑ ዋና በር ላይ ቆመው እየጠበቁን እንደነበር ስንመለከት ወደዚያው አቀናን፡፡ እንኳን ደህና መጣችሁ በሚል ፈገግታ የተቀበሉን ካህናት በእድሜ ጸና ያሉ ናቸውና እድሜ የሰጣቸው ጸጋ እና ክህነት የሰጣቸው ክብር ከብዶን አብዝተን ተጎነበስን፡፡ ተባርከን እና ተዋውቀን ከቤተ ክርስቲያኑ ጥግ ትንሽ እረፍት አደረግን፡፡ በዚህ መቆየት እንዴት ደስ ይላል፤ ግሳንግስ ከበዛባት ዓለም ርቆ ስጋንም መንፈስንም በጸጥታ መመልከት ቃላት የማይገልጹት የተለየ የደስታ ስሜት አለው፡፡
ከ400 ዓመታት በላይ የዘለቀ እድሜ ያለው የቤተ ክርስቲያኑ አካባቢ ሁለት የተለያዩ ጊዜያትን አስተናግዷል ይባላል፡፡ ቀድሞ የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የነበረበት ይህ እድሞ የበርካታ ታላላቅ አባቶች አጽም ያረፈበት፤ እምነት እና ታሪክ የተንሰላሰሉበት ቦታ ነበር አሉ፡፡ የቅዱስ ሚካኤል ጽላት እና ቤተ ክርስቲያን ከዚህ አካባቢ ተነስቶ ወደ ማይ ጥምቀት መሄዱን ተከትሎ አካባቢው እስከ 1933 ዓ.ም ድረስ ኦና ደብር ሆኖ ቆይቶ ነበር ይባላል፡፡
1933 ዓ.ም ላይ የአካባቢው መሳፍንት፣ መኳንንት እና ሕዝቡ የቀደሙ አባቶቻችን አጽም ካረፈበት ቦታ ላይ ቤተ ክርስቲያን ሊጸና ይገባል በማለታቸው በእለተ ቅዳሜ ጥቅምት 9/1933 ዓ.ም ደብረ ገነት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተባርኮ ገባ ይሉናል የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መልዓከ ገነት ቄስ መርከብ መንግሥቱ፡፡
አካባቢው በወቅቱ በጎንደር ጠቅላይ ግዛት በወገራ አውራጃ በወልቃይት ወረዳ የሚገኝ ቀበሌ ነበር የሚሉት ዋና አስተዳዳሪው 1980ዎቹ መጀመሪያ ወደ ትግራይ በኃይል እስኪካለል ድረስ አባቶቻችን ለአቤቱታም ሆነ ለመንግሥት አገልግሎት የሚያቀኑት ወደ ዳባት እንደነበር አስታውሳለሁ ብለውናል፡፡
“ሆዴ አያሌው ሸር ያለው፤ ር ያለው” በአካባቢው ወጣቶች የሚዘወተር ዓለማዊ ዘፈን ነበር የሚሉት መልአከ ገነት ቄስ መርከብ በወቅቱ ደጃዝማች አያሌው ብሩ የወገራ አውራጃ አስተዳዳሪ ስለነበሩ እርሳቸውን እያወሱ የሚዘፈን ነበር ይላሉ፡፡ ከልጅነታችን ጀምሮ አካባቢው በጎንደር ጠቅላይ ግዛት እንደሚተዳደር በርካታ ማስረጃዎች አሉ፡፡
ቄስ መርከብን ጨምሮ በርካታ የአካባቢው ቀሳውስት እና ዲያቆናት ዲቁና እና ክህነት ለመቀበል ወደ አክሱም ያቀኑ እንደነበር ገልጸው በ1966 ዓ.ም ገደማ ዲቁና ለመቀበል አክሱም ሄደው በወቅቱ ከነበሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዮሐንስ ዘንድ የተቀበሉት የዲቁና መረጃ በበጌምድር ጠቅላይ ግዛት በወገራ አውራጃ በወልቃይት ወረዳ በኩሊታ ብላምባ ቅርሽ ደብረ ገነት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ስለመማራችን የሚገልጽ ነበር ይላሉ፡፡
በ1968 ዓ.ም የአካባቢው ተወላጅ እና መስፍን የነበሩት ባላምባራስ ሲሳይ ገዛኽኝ አክሱም ደረስ ዘልቀው ያሰሩት የወርቅ መስቀል ዛሬም ድረስ በቤተ ክርስቲያኑ ይገኛል፡፡ የወርቅ መስቀሉ የተሰራው አክሱም ውስጥ የሚገኝ የአካባቢው ተወላጅ እና ቀራጺ ባለሙያ በነበረው ገሠሠ ባስልኤል ሲሆን በወርቅ መስቀሉ ላይ የሰፈረው መልዕክትም “በጎንደር ጠቅላይ ግዛት ወልቃይት ዘ ታቦተ መድኃኔዓለም ኩሊታ ብላምባ ቅርሽ” ባላምባራስ ሲሳይ ገዛኽኝ ስመ ጥምቀት ገብረ ህይዎት ይላል፡፡
ይኽ ሁሉ የማንነታችን አካል ነው የሚሉት የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ማንነት ቢፍቁት የማይለቅ ማህተም በመሆኑ አማርኛ እንዳይነገር ብዙ ቢሠራም የተፈለገውን ያክል ለውጥ ማምጣት ግን አልተቻለም ነው ያሉት፡፡
ሃይማኖት ድንበር የለውም በእኛ ዘመን አክሱም ድረስ ተጉዘን ዲቁና እና ቅስናን እናመጣ ነበር የሚሉት መልአከ ገነት የሁለቱን ወንድም ሕዝቦች መልካም ግንኙነት የሚያሻክር ድርጊት መፈጸሙ ተገቢነት አልነበረውም ይላሉ፡፡
በርካታ አስርት ዓመታትን የህይወት መሥዋትነት እየከፈልን ማንነታችን ለማጽናት ታግለናል፣ ብዙ መከራና ግፍም አሳልፈናል፤ አሁን የተገኘው ነፃነትም ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል ነው ያሉን የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መልዓከ ገነት ቄስ መርከብ መንግሥቱ።
“ስለወልቃይት አማራነት አክሱም ሳይቀር ምስክር ናት!”
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!