
ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የክረምት ወቅታዊ የግብርና ሥራዎችን አስመልክቶ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና ሥርጭት ላይ በታዩ ችግሮች ላይ ነው ውይይት የተደረገው።
የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም እና የቀረበውን ግብዓትም ፍትሐዊ በኾነ መንገድ የማሰራጨት ችግር ማጋጠሙን የቢሮው ኀላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) ገልጸዋል።
ከወደብ የደረሰውንም በፍጥነት ወደ ክልሉ የማጓጓዝ እና ክልሉ ላይ ከደረሰ በኋላም ለአርሶ አደሮች በፍትሐዊነት የማዳረስ ችግር መኖሩን አንስተዋል።
በተለይም በአንዳንድ ዞኖች አንዳንድ ባለሃብቶች፣ ነጋዴዎች፣ ደላሎች፣ የሥራ ኀላፊዎችና ባለሙያዎች ጭምር በስርቆት መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
በሕገወጥ ሥራ ላይ በተሰማሩ ግለሰቦች ላይም ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መኾኑን አንስተዋል።
አሁንም ዘግይተው ለሚዘሩ ሰብሎች የቀረበውን የአፈር ማዳበሪያ በፍትሐዊነት ማሰራጨት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው እንደገለጹት ደግሞ በክልሉ በሕገ ወጥ የአፈር ማዳበሪያ ዝውውር የተሳተፉ 282 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
4 ሺህ 648 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያም ተይዟል ነው ያሉት። በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ውስጥ በ10 ሰዎች ላይ ውሳኔ ተሰጥቷል፤ በ17 ሰዎች ላይ ክስ ተመሥርቷል፤ 54 ሰዎች ደግሞ በፖሊስ ምርመራ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ አሁንም ሕገወጥነትን ተከታትሎ አለማስቆም፣ እጥረቱን ለመፍታት የአፈር ማዳበሪያ ክምችት ካለባቸው አካባቢዎች እጥረት ወደ አለባቸው አለማሰራጨት እና ችግር ያለባቸውን ግለሰቦች እርምት ያለመውሰድ ችግሮች እንዳሉ አንስተዋል።
በቀረበው የማዳበሪያ የፍትሐዊነት ስርጭትና ሕገወጥ ድርጊት ተጠያቂው ክልሉ ቢኾንም ግብርና ሚኒስቴር በቂ ግብዓት በወቅቱ ባለማቅረቡ ለተፈጠረው ችግር ኀላፊነት ሊወስድ እንደሚገባም ተሳታፊዎች አንስተዋል።
በቀጣይ የምርት ዘመንም ተመሳሳይ ችግር እንዳያጋጥም ከወዲሁ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ላይ ሰፊ ዝግጅት ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!