
ሁመራ: ሐምሌ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የዳንሻ ከተማ አሥተዳደር ከ29 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ ያስገነባቸውን የመሠረተ ልማት ሥራዎች አስመርቋል። ላለፉት ሦስት ዓመታት የፌደራል በጀት የሌለው ዞኑ እና ከተማ አሥተዳደሩ ከሕዝብ፣ ከውስጥ ገቢ እና ከአጋር አካላት በተገኘ ገንዘብ የመሠረተ ልማት ጅምሮችን ማሳካት ችሏል ተብሏል።
ነጻነት እና እኩልነት፣ ሠላም እና አንድነት፣ ብዝሐነት እና መቻቻል የዳንሻ ከተማ መለያ እሴቶች ናቸው ያሉት ከንቲባ አብዱለሃብ ማሙ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ ስሁት ክስተቶች እሴቶቻችንን በአግባቡ እንዳንጠቀም አድርገውን ቆይቷል ብለዋል። በሕዝብ ትብብር የተገኘው ነጻነት ፍትሐዊ የመልማት አጋጣሚዎችን በአግባቡ ለመጠቀም እድል እንደፈጠረም ከንቲባው አንሰተዋል።
ሕዝቡ በእኩል የማደግ መብቱ ተነፍጎት፣ በባሕሉ እንዳይደምቅ፣ በእሴቱ እንዳይጠቀም እና በማንነቱ እንዳይኮራ ተደርጎ ቆይቷል ያሉት ከንቲባው ያለፉትን ሦስት ዓመታት አንጻራዊ መረጋጋት እና ሠላም ተጠቅሞ በራሱ አቅም ያለማቸውን የመሠረተ ልማት ሥራዎች በደመቀ መልኩ ለማስመረቅ በቅቷል ነው ያሉት።
ወያኔ በከተማዋ ለዘመናት የዘረጋው ብልሹ እና ኅላፊነት የጎደለው አሠራር አለመረጋጋት እንዲስፋፋ፣ በሕዝብ መካከል ጥርጣሬ እንዲሰፍን፣ ማንነትን መሠረት ያደረገ አድሎ እና መገለል እንዲፈጸም አድርጎ ቆይቷል ተብሏል። ይህም ማዕከል የኾነችውን ተስፈኛ ከተማ ተስፋ የሌላቸው ነዋሪዎች እንዲበዙባት እና ተመርረው እንዲለቁ ታስቦበት የተሠራ እንደኾ አንስተዋል።
ለ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የማይመጥነው የከፋፍለህ ግዛ መንግሥታዊ መርሕ ከተማዋ በዝባዦችን እና አቆርቋዦችን አቅፋ እንድትዘልቅ አድርጎ ቆይቷል ያሉት ከንቲባ አብዱለሃብ ምዝበራው ድርጅታዊ እና መዋቅራዊ ነበር ብለዋል። ያንን ሁሉ ግፍ እና ጭቆና ከመላው ኢትዮጵያዊያን ጋር በመታገል እና በመጣል ለዛሬው ድርብ ድል በቅተናል ነው ያሉት።
ላለፋት ሦስት ዓመታት ያለምንም መንግስታዊ በጀት የመንግሥት ተቋማትን በብቃት መምራት እና ማዝለቅ ተዓምራዊ ነው ያሉት ከንቲባው በራስ አቅም መልማት እንደሚቻል አይተናል ብለዋል። ከሕዝብ፣ ከውስጥ አቅም እና ከአጋሮቻችን በተሰበሰበ 29 ሚሊዮን 727 ብር የጌጠኛ መንገድ ግንባታ፣ የጥርጊያ መንገድ ግንባታ፣ ጥገና እና የተፋሰስ ቦይ ግንባታ ተካሂዷል ብለዋል።
“የሕዝብን አቅም እና ጉልበት በመጠቀም ብቻ በከተማ አሥተዳደሩ እና በዞኑ በርካታ የለውጥ ጅምሮች ታይተዋል” ያሉት ከንቲባ አብዱለሃብ ማሙ ሕዝቡ ለዘመናት የጠየቀውን ሕጋዊ የማንነት ጥያቄ እና በጀት መመለስ ተገቢ መኾኑንም አንስተዋል። ለቀጣይ ዓመታት በእቅድ የተያዙ የመሠረተ ልማት ሥራዎች መኖራቸውን ያነሱት ከንቲባው ዳንሻን በሚገባት ልክ ለማልማት ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!