
ሁመራ: ሐምሌ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዳንሻ ከተማ አሥተዳደር ከ29 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ ያስገነባቸውን የመሠረተ ልማት ሥራዎች እያሰመረቀ ነው። የመሠረተ ልማት ሥራዎቹ ግንባታ ከነጻነት ማግስት የተገኙ ተስፋ ሰጭ ጅምሮች ናቸው ተብሏል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኅላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ከነጻነት ማግስት ዳንሻ ከተማ አሥተዳደር በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ሥራ ተሰርቶላት ማየት የተለየ ስሜት አለው ብለዋል።
የታገላችሁት እና ዋጋ የከፈላችሁት ፍትሐዊ የልማት እድል ለማግኘት ነበርና እንኳን ደስ አላችሁም ብለዋል።
ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በዳንሻ ሕዝብ ስም በየዓመቱ በጀት ይመደባል፤ ነገር ግን ለከተማዋ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ እንኳን አልተሠራም ብለዋል። በየዓመቱ ሰኔ እና ግንቦት ላይ የተመደበ በጀት አልቋል እየተባለ የድጎማ በጀት ሳይቀር የተጠየቀባት ከተማ የለማውን መሠረተ ልማት እናንተም እኛም ያየነው ነበር ነው ያሉት።
ኮሎኔል ደመቀ የኑሮ ውድነትን ጨምሮ በርካታ ማኀበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ባሉበት በዚህ ወቅት በራስ አቅም እና ተነሳሽነት የመሰረተ ልማት ሰርቶ ማጠናቀቅ ተዓምር ነው ብለዋል።
የከተማዋ ወጣቶች የነጻነት ብቻ ሳይኾን የልማት ተምሳሌት እና ተስፋ ናችሁ ያሉት ኮሎኔል ደመቀ ከዚህ በኋላ ያለው ዘመን እና ኅላፊነት የእናንተ በመኾኑ ራሳችሁን አዘጋጁ ብለዋል።
አሁን ያለው ትውልድ የወያኔን ግፍ እና በደል አምርሮ በመጥላቱ ታግሎ እና አታግሎ ከዚህ ደርሷል ነጻነቱን ማዝለቅ እና ማጽናት ደግሞ በትውልድ ቅብብሎሸ የሚገነባ ነው ብለዋል።
ትናንት አባቶቻችን፣ እናቶቻችን፣ እህቶቻችን እና ወንድሞቻችን በወያኔ ያ ሁሉ መከራ እና ግፍ የደረሰባቸው ደካማ ኾነው ሳይኾን ሁሉን በማመን ተዘናግተው ስለነበር ነውም ብለዋል። ያንን ስህተት ዳግም መድገም ትውልድን ለማያቋርጥ እልቂት መዳረግ በመኾኑ ያገኘናትን እያንዳንዷን አጋጣሚ በተገቢው መንገድ መጠቀም ይገባል ብለዋል ኮሎኔል ደመቀ።
የአካባቢው ሕዝብ ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎች አሉት ያሉት ኮሎኔል ደመቀ የማንነታችን ሕጋዊ እውቅና እና ተፈጥሯዊ የኾነው የበጀት መብት ናቸው ብለዋል። የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ በሕዝብ መስዋእትነት ተመልሷል። ጥያቄያችን እውቅና በመኾኑ እውቅናውን እስክናገኝ ድረስ እየሠራን እናሳያቸዋለን ነው ያሉት።
የሕዝብ ጥያቄ እስኪመለስ ድረስ አሥተዳደሩ እና ሕዝቡ በጋራ መቆም፣ አንድ መኾን፣ መሰባሰብ እና መደማጥ ያስፈልጋል ተብሏል። አሁን እያየናቸው ያሉ ለውጦች በጋራ በመቆማችን ያመጣናቸው ናቸው ያሉት ኮሎኔል ከትናንቱ የተሻለ ነገን ለማምጣት ቀን ከሌሊት መሥራት ይጠይቃል ነው ያሉት።
“ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት አስመጋቢዎች እንጂ ተመጋቢዎች አልነበርንም” ያሉት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በጋራ መሥራት እንደሚገባ መልእክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!