ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች እያስመረቀ ነው።
የእለቱ የክብር እንግዳና የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ከፍያለው ዓለማየሁ ሀገር የሚረከብን መልካም ዜጋን የማፍራት ከባድ ኀላፊነት የተሸከመው የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ኀላፊነቱን በልኩ እየተወጣ ስለመኾኑ አስረድተዋል።
ፕሮፌሰር ከፍያለው እንዳሉት ተማሪዎች የሚጠበቅባቸውን እውቀት ፣ክህሎትና አመለካከት እንደሰነቁ የወሰዱት የመውጫ ፈተና ውጤት ጉልህ ማሳያ ነው ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ስኬታማነት የሚረጋገጠው ተመራቂ ተማሪዎች በሥራቸው፣ በማኅበራዊ ሕይዎታቸው በሚያስመዘግቡት ውጤት ነው ያሉት ፕሮፌሰር ከፍያለው ለዚህም ተመራቂዎች ሀገራዊ ኀላፊነታቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸውም ነው የተናገሩት።
የዛሬ ተመራቂዎች ሀገር ፍቅርን፣ መተሳሰብንና አንድነትን በምትሻበት ወቅት፤ ለእውነት መታገል የሕልውና ጉዳይ በኾነበት ወቅት የተመረቃችሁ መኾኑን ልብ በሉ ብለዋል።
ፕሮፌሰር ከፍያለው አለማየሁ ተመራቂዎች በቀጣይ ከወገናቸው ጎን በመኾን የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው ባገኙት እውቀት፣ በቀጣይ በሚሰማሩበት ሙያ ሁሉ ሀገርና ሕዝብን በታማኝነትና በዕውቀት እንዲያገለግሉ አደራ ብለዋል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!