“ዘርፈ ብዙ ችግር በያዘች ሀገር የሚያስፈልጋት ዘርፈ ብዙ መፍትሔ ነው” ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው

46

ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አዳማ ዩኒቨርሲቲ ለቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል፡፡ ቀዳማዊት እመቤቷ የክብር ዶክትሬት የተሰጣቸው በኢትዮጵያ በማኅበራዊ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽዖ ነው ተብሏል፡፡
የክብር ዶክትሬቱን የተቀበሉት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ በመልእክታቸውም ለተሰጣቸው ክብርና እውቅና አመስግነዋል፡፡

አሁን ወደአሉበት ኃላፊነት ከመጡ ጀምሮ ሁለት ነገሮች ላይ ትኩረት እንዳደረጉ የተናገሩት ቀዳማዊት እመቤቷ ትምህርትና የዳቦ አቅርቦት ደግሞ ትኩረት ያደረጉባቸው መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡
አንድ የተቸገረ ሰው ዳቦ ማግኘት ከቻለ ለከፋ ችግር አይጋለጥም፣ መሥራትም ኾነ መማር ይቻለዋል ነው ያሉት፡፡

ብዙዎች የኢትዮጵያ ልጆች አንጀታቸውን አስረው የተማሩ ናቸው ያሉት ቀዳማዊት እመቤቷ ቆሎ እየበሉ፣ በቀን አንድ ጊዜ ጭብጦ እየተመገቡ የተማሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

በርካቶች ድህነትን ያሸነፉት በትምህርት ነው፣ እነዚህ ጀግኖች ካልጠገብን አንማርም ቢሉ ኖሮ ትምህርቱንም፣ ጥጋቡንም ማግኘት አይችሉም ነበርም ነው ያሉት፡፡ ያገኙትን ቁራሽ በልተው ተግተው በመማራቸው ድህነትን በእውቀት አሸንፈውታል ብለዋል፡፡ ትምህርት ላይ ያተኮርነው ትምህርት ድህነትን ማሸነፊያ ትልቁ መሳሪያ ስለኾነ ነውም ብለዋል፡፡

ትምህርት ቤቶችን በተሻለ ደረጃና ጥራት ሰርተን ላልደረሳቸው ብናደርሰ ድህነትን የሚያሸንፉ፣ ብዙ ኢትዮጵያውያን ማፍራት እንችላለን ነው ያሉት፡፡

ዘርፈ ብዙ ችግር በያዘች ሀገር የሚያስፈልጋት ዘርፈ ብዙ መፍትሔ ነውም ብለዋል፡፡ ደሃ ተኮር ተግባር የሁሉንም እርብርብ እንደሚፈልግም አስገንዝበዋል፡፡ ድሆችን መመገብ፣ ትምህርትና ጤናን ማዳረስ ከፖለቲካ ዓላማ በላይ መኾናቸውን እና የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ዓላማ መኾናቸውን ነው የገለጹት፡፡ በየትኛውም ደረጃና አቅም ያለ ሁሉ የድሆችን መመገቢያዎች እንዲያስፋፋ፣ ትምህርትና ጤናን እንዲያበዛ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን አቅማችንን ማስተባበር ከቻልን፣ የብዙዎችን ችግር እንቀርፋለን፣ የብዙዎችን እንባ እናብሳለን፣ የብዙዎችን ሕልም እናሳካለን፣ ኢትዮጵያውያን ይህን እንደምናደርግ እምነቴ ነውም ብለዋል፡፡ ለማይጠቅመን እያዋልነው ያለውን ሀብት፣ ጊዜና እውቀት ኢትዮጵያን ለሚገነባ ተግባር እንድናውለው አደራ እልላሁ ነው ያሉት፡፡

የተሰጣቸው ክብር አብረዋቸው ለሠሩት ሁሉ የተሰጠ ክብር መኾኑንም አንስተዋል፡፡

ለተማሪዎች ባስተላለፉት መልእክት ቤተሰቦቻችሁ ወልደው አሳድገው እዚህ አድርሰዋል ፤ እንደገና ተጧሪ እንዳትኾኑ ባገኛችሁበት የሥራ ዘርፍ ተሰማርታችሁ ቤተሰቦቻችሁን እንድታሳርፉ አደራ እላለሁም ብለዋቸዋል፡፡ ሀገራቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉም አደራ ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጠንካራ ጋዜጠኝነት ተምሳሌቷ እና የባለታሪኮች ባለአደራ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ለዚህ ታላቅ ክብር በመብቃትሽ እንኳን ደስ አለሽ!
Next article“የተመረቃችሁት ለእውነት መታገል የኅልውና ጉዳይ በኾነበት ወቅት ነው” ፕሮፌሰር ከፍያለው ዓለማየሁ