የጠንካራ ጋዜጠኝነት ተምሳሌቷ እና የባለታሪኮች ባለአደራ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ለዚህ ታላቅ ክብር በመብቃትሽ እንኳን ደስ አለሽ!

75

ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2015 ዓ.ም የተማሪዎች ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ለአንጋፋዋ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ የጠንካራ ጋዜጠኝነት ተምሳሌት እና የባለታሪኮች ባለአደራ በሚል የዓመቱን የአርት የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷታል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሰቲ ሴኔት በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1152 / 2011 በተሰጠው ስልጣን መሰረት በአርት የዓመቱ የክብር ዶክትሬት ለአንጋፋዋ ጋዜጠኛ ማዕዛ ብሩ እንዲሰጣቸው ወስኗል፡፡ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ የጥንካሬ ተምሳሌትና በዘርፉ ለበርካቶች አርአያ ስለመኾኗ ተገቢ እውቅና ይኾን ዘንድ ነው ዮኒቨርሲቲው የዓመቱን የአርት የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የሰጣት ፡፡

ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል ኤፍ ኤም ሬዲዮ የሸገር መስራች እና ባለቤት፤ የመጀመሪያዋ ሴት የሬዲዮ ማሰራጫ ድርጅት መስራችና ባለቤት፤ በእንግዶች ምርጫዋ፤ በምርምር በተደገፈ የመጠይቅ ዘይቤዋ፣ በትህትናዋ፣ በአነጋገር ለዛዋ በቀጥታ አዘጋጅታ ከምታቀርባቸው ፕሮግራሞች (የቅዳሜ ጨዋታ እና ሸገር ካፌ) በተጭማሪ በተለያዩ የሸገር ሬዲዮ ፕሮግራሞች እንዲሁም በሌሎች ሬዲዮም ኾነ ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ አሻራ የተወች እና በጋዜጠኝነት ዘርፍ ለተሰማሩ ጋዜጠኞች አርአያ መኾኗ ለሽልማት እንዳበቃት ዮኒቨርሲቲው አስታውቋል፡፡

ከሥራዎቿ ውስጥ በርካታ ባለታሪክ ምሁራን፣ የመንግስት ሥራ ኀላፊዎች፤ የኪነ-ጥበብ ሰዎች፤ ጋዜጠኞች እና ሌሎች ባለሙያዎች የህይወት ታሪክ፤ ሥራ ፣ አስተሳሰብ እና ለሌሎች አርአያ የሚኾነውን የሕይዎት ፍልስፍናቸው በራሳቸው አንደበት ተሰናድቶ ለታሪክ እንዲቆይ ማድረጓ በዋናነት ተጠቅሷል።
የጨዋታ እንግዳ መሰናዶዋ እንግዶቿ ያካበቱት ልምድ፤ አበርክቶታቸው፤ ያልተጻፉ ሀገራዊ ጉዳዮች እና ሚስጥሮች ከኃላፊ ባለታሪኮቹ ጋር እንዳያልፉ፤ በመቅረጸ ድምጽ ተሰንቀው በሰፊው እንዲታወቁ እና ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፉ ማድጓም ለክብር ዶክትሬት ዲግሪ ለመሸለሟ ሌላው ምክንያት ነው ተብሏል።

በ1950ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ የተወለደችው ጋዜጠኛ መዓዛ እስከ ዘጠኝ ዓመቷ ድረስ በምዕራብ ሐረርጌ በምትገኘው ሂርና ከተማ አደገች። ሂርና ሳለች ጎረቤቶቿ የኦሮሞ፣ የሃረሪና የሶማሌ የየመን ተወላጆች ስለነበሩ በተለያዩ ባሕላዊ እሴቶች እና እርስ በእርስ ትስስር የዳበረ አስተዳደግ ነበራት። ይህም፣ ለሥነ-ጽሁፍ ከነበራት ዝንባሌ ጋር ተዳምሮ ለዛሬው ማንነቷ መሰረት እንደኾናት ይነገራል።

ጋዜጠኛ መዓዛ በዘጠኝ ዓመቷ ወላጆቿ አዲስ አበባ ወደ ሚገኘው የቅድስተ ማርያም የልጃገረዶች ካቶሊክ አዳሪ ትምህርት ቤት አስገቧት፡፡ በ1967 ዓ.ም የሁለትኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለች በእድገት በኀብረት ዘመቻ ወደ ውቅሮ ትግራይ ተልካ ለስድስት ወራት አገልግላለች። በ1970 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብታ በሥነ ልሳን ትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች።

ከሬዲዮ ጋዜጠኝነት ሥራን በአጋጣሚ እንደጀመረች የሚነገርላት ማዕዛ በወቅቱ ተወዳጅ ከነበረው የእሁድ ፕሮግራም ጋር ለስምንት ዓመታት ያክል ሠርታለች፡፡

በመጀመሪያ በቋሚነት የተመደበችበት ሥራዋ በባሕል ሚኒስቴር ሥር የመርሐ ስፖርት ጋዜጣ የስፖርት ዘጋቢነት ነበር። በመቀጠልም በኢትዮጵያ ሬዲዮ የእሁድ ፕሮግራም ተሳትፎዋን ሳታቆም በባሕል ሚኒስቴር የአለም አቀፍ አግልግሎት ክፍል አገልግላለች፡፡ ከዚያም በብሔራዊ ባንክ የብሪቱ መጽሄት ዋና አዘጋጅ በመኾን የፋይናንስ ዜናዎችን እና አጫጭር ታሪኮችን በመጻፍ እና በአርትኦት አገልግላለች፡፡

በ1984 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ተቀላቅላ የፕሬስ እና ኮሚኒኬሽን ኦፊሰር በመኾን ለአራት ዓመታት ሰርታለች፡፡ ከዚያም በግል በአማካሪነት እና በሕዝብ ግንኙነት እና ማስታወቂያ ስትሠራ ከቆየች በኋላ በ1987 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሬዲዮ በ97.1 የሬዲዮ ጣቢያን የአየር ሰዓት በመጠቀም የቅዳሜ ከሰዓት የጨዋታ ፕሮግራምን ከባለቤቷ ከአርቲስት አበበ ባልቻ እና ከረዥም ጊዜ ጓደኛዋ አርቲስት ተፈሪ አለሙ ጋር የማዘጋጀት ዕድል አግኝታ ፕሮግራሙን ለስምንት ዓመታት ያክል ስታቀርብ ቆይታለች ። በመጨረሻም በ2000 ዓ.ም ተወዳጅ የኾነውን ሸገር ኤፍ ኤም 102 ነጥብ 1ን ለመመስረት በቅታለች።

ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ የጥንካሬ ተምሳሌትና በዘርፉ ለበርካቶች አርአያ ለመኾኗ ተገቢ እውቅና ይኾን ዘንድም የባሕር ዳር ዩኒቨርሰቲ ሴኔት በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1152 / 2011 በተሰጠው ስልጣን መሰረት በአርት የዓመቱ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷታል፡፡
የጠንካራ ጋዜጠኝነት ተምሳሌቷ እና የባለታሪኮች ባለአደራ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ለዚህ ታላቅ ክብር በመብቃትሽ እንኳን ደስ አለሽ!

ዘጋቢ፡- ፋሲካ ዘለዓለም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ የክብር ዶክትሬት ድግሪ ሰጠ፡፡
Next article“ዘርፈ ብዙ ችግር በያዘች ሀገር የሚያስፈልጋት ዘርፈ ብዙ መፍትሔ ነው” ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው