“ውድ ተመራቂዎቻችን ባገኛችሁት እውቀት ሕዝባችሁንና የጋራ ቤታችሁን ኢትዮጵያን እንድታገለግሉ፣ እንድትጠብቁም አደራ እላለሁ” ዶክተር ታምሬ ዘውዴ

40

ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች እያስመረቀ ነው።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ታምሬ ዘውዴ (ዶ.ር) በተማሪዎች ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳሉት በዛሬው የምረቃ መርሐ ግብር በተለያዩ የትምህርት መስኮች 521ተማሪዎች ተመርቀዋል።

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ዛሬ 4ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ነው የሚያስመርቀው ። ባለፉት ሦስት ዙሮች ከ2 ሺህ 334 ተማሪዎችን እንዳስመረቀም ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ ለተማሪዎች እንዳሉት ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን ሁሉ የዛሬ ተመራቂ ተማሪዎችም ፈተናዎችን ሁሉ አልፋችሁ ለስኬት በቅታችኋልና እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

ዶክተር ታምሬ ለተመራቂ ተማሪዎች ባስተላለፉት መልእክት ትምህርት የኢኮኖሚያዊ፣የማኀበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች መፍቻ ቁልፍ መሣሪያ ነውና በተማራችሁት ትምህርት ሀገራችሁን እንድታገለግሉም አደራ እላለሁ ብለዋል፡፡

የምንገኝበት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ኹኔታ በበርካታ ፍላጎቶችና ጫናዎች ውስጥ የወደቀ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ የዛሬ ተማራቂዎች ሀገር የምትኮራባቸው እንዲኾኑም በአጽንኦት አሳስበዋል።

“ውድ ተመራቂዎቻችን ባገኛችሁት እውቀት ሕዝባችሁንና የጋራ ቤታችሁን ኢትዮጵያን እንድታገለግሉ፣እንድትጠብቁም አደራ እላለሁ” ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ዶክተር ታምሬ ዘውዴ።

መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ በትምህርትና ምርምር ፣በማኀበረሰብ አገልግሎት ይተጋል፣ በገበያው ተፈላጊ የኾኑ ብቁ ተማሪዎችን እያሰለጠነ ለሀገር ያበረክታልም ብለዋል ዶክተር ታምሬ።

ዘጋቢ፦ ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ማንኛውም ስኬት የሚገኘው ፈተናን ተጋፍጦ በማለፍ ብቻ ነው” ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)
Next articleዶክተር ፍሬው ተገኝ ተመራቂ ተማሪዎች በተማሩበት የትምህርት ዘርፍ ያስተማራቸውን ኅብረተሰብ በቅንነት እና በታማኝነት እንዲያገለግሉ አሳሰቡ።