
ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን እያስረቀ ነው፡፡ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)፣ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፍሬው ተገኘ (ዶ.ር) እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ተመራቂ ተማሪዎች እና ለተመራቂ ተማሪ ወላጆች የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ርእሰ መሥተዳድሩ በመልእክታቸው ባሕርዳር ዮኒቨርሲቱ ላፉት 60 ዓመታት ለሀገር ብቻ ሳይኾን ለዓለም እውቀትን ለማስፋት የሚተጉ፣ ልማትን ለማሳደግ የሚሠሩ፣ የሰውን ሕይወት ለማሻሻል የተጉ ብቃት ያላቸው ሰዎችን በማፍራት አስተዋጽዖ አበርክቷል ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በማስተማር፣ በምርምር እና በማኅበረሰብ አገልግሎት ተልዕኮን ለመወጣት እየሠራ የሚገኝ አንጋፋና ተመራጭ ተቋም ኾኗል ነው ያሉት፡፡ የዩኒቨርሲቲው ተልእኮ የሚሳከው በትጋት በሚተጉ መምህራን፣ ተማሪዎች ትጋትና ተቋርቋሪነት ነውም ብለዋል፡፡ ዮኒቨርሲቲው ለሀገር እያደረገው ያለው አስተዋጽዖ የሚደነቅና የሚበረታታ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው እውቀትን እያሰፋ፣ ምርምርን እያሳደገ፣ ቴክኖሎጂውን እያስተዋወቀ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው እስካሁን ተመራጭ ኾኖ የቆየበትን እንደ ስንቅ በመውሰድ በቀጣይም ጠንክሮና አስፍቶ መሥራት አለበት ነው ያሉት፡፡ ዩኒቨርሲቲው ተመራጭ እንዲኾን የሠሩ ሁሉ ወደፊትም በትጋት እንዲሠሩም አሳስበዋል፡፡
እውቀት ለመሸመት፣ ክህሎት ለማሳደግ የራስን ጥረት ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡ ተማሪዎች በራሳቸው የሚተማመኑ፣ እውቀት ያላቸው፣ በሰለጠኑበት ሙያ ሁሉ ሲሰለፉ የሚፈለገውን አስተዋጽዖ ለማድረግ የራስ ተነሳሽነታቸውን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
በራስ የመተማመን ስሜትን ለመፍጠር የራስን አቅም ማሻሻል እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ ተማሪዎች ለመመረቅ የበቁት ከፍተኛ ውጣ ወረዶችም በማለፍ እንደኾነ ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ የኮሮና ቫይረስን እና በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት ተቋቁመው ለመመረቅ መብቃታቸውን ነው የገለጸት፡፡ ፈተናዎችን ተቋቁመው የተመረቁ ተማሪዎች ፈተናን በትዕግሥት፣ በጽናት እና በጥበብ የማለፍን ልምደ እንዳገኙም አንስተዋል፡፡
ተማሪዎች የመጀመሪያውን የሕይወት ምዕራፍ አጠናቀው ቀጣዩ የሕይወታቸው ምዕራፍ መጀመሪያ ላይ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎች ከትምህርት ሕይወታቸው የበለጠ ፈተና ሊገጥማቸው እንደሚችልም አስገንዝበዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የቀጣይ ሕይወታቸው ያመረ እንዲኾን ጥበብና ስልት ያስተምራችኋል እንጂ በቀጣይነት ያለው ሕይወታቸው በራሳቸው ብርታት ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋቸዋል፡፡
ሕይዎት ዘርፈ ብዙ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ሕይወታችሁን የምትመሩበት የተለያየ አጋጣሚ ይኖራል፣ ራሳችሁን፣ ቤተሰባችሁን እና ሀገራችሁን የሚጠቅም ስራ እንደምትሠሩም እናምናለን ነው ያሏቸው፡፡ ሀገር የሚገነባው ትውልዱ በሚያበረክተው የተቀናጀና የተናበበ አስተዋጽዖ ድምር ውጤት ነውም ብለዋል፡፡
ሀገር የሚገነባው በትውልድ ነው፣ ተመራቂ ተማሪዎችም ሀገራቸውን በማገልገል ስኬታማ እንደሚኾኑም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ ሕይወታችሁ የሚያጋጥማችሁን ፈተና በስሜት ሳይኾን በስክነት፣ በጉልበት ሳይኾን በጥበብ እና እውቀት እንደምትሻገሩ እናምናለንም ብለዋል፡፡ በስክነት እና በብስለት ከሄዱ ሀገር የገጠማትን ውስብስብ ችግር በመግታት እና በመፍታት ወደ ተሻለ ሰላምና ልማት እንደሚያሻግሯትም ገልጸዋል፡፡
የነገ ሕይወታችሁ የሚሰምረው በራሳችሁ ፍላጎትና ቁርጠኝነት ነውም ብለዋቸዋል፡፡ ማንኛውም ስኬት የሚገኘው ፈተናን ተጋፍጦ በማለፍ ብቻ ነውም ብለዋል፡፡ ስኬት ዝም ብሎ የሚገኝ እርካሽ ነገር አይደለም፣ መስዋእትነት የሚጠቅይ፣ ያለመሰልቸትና ያለመታከት ሳይደክሙ መሥራትን የሚጠይቅ ተግባር ነውም ብለዋል፡፡ የተማሪዎች ስኬት የዩኒቨርሰቲው ስኬት መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!