
ደብረ ብርሃን: ሐምሌ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ፣ መርሀቤቴና ሚዳ ወረደሞ ወረዳዎችን የሚያገናኘው የጀማ ወንዝ የብረት ድልድይ ተሰብሮ የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡን አሚኮ ዘግቦ ነበር።
ይህ ድልድይ ከአዲስ አበባ በሚዳ ወረደሞ መርሀቤቴ በኩል እስከ ደሴ የሚያገናኝ ነው። ከደብረ ብርሃን ወደ መርሀቤቴ ፣ ሚዳና ወረኢሉ ለመጓዝም ያገለግላል። አልፎ አልፎ ወደ መንዝ ቀጠና ለሚደረግ የትራንስፖርት እንቅስቃሴም እንደ አማራጭ ይጠቀሙበታል።
ይህ የብረት ድልድይ ሁለት ሲኖትራክ ተሽከርካሪዎች በተመሳሳይ ጊዜ ወደ ድልድዩ መግባታቸውን ተከትሎ ተሰብሮ ነበር። አሁን ላይ ግን ሙሉ ጥገና ተደርጎለት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። ድልድዮ 100 ሜትር ገደማ ርዝመት አለው። ከዚህ ቀደም 3 ነጥብ 2 የነበረው ስፋቱም ወደ 4 ነጥብ 2 ሜትር እንዲሻሻል ተደርጓል።
ጥገናውን በኢትዮጵያ መንገዶች አስሥተዳደር የአለም ገና ዲስትሪክት ከቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ጋር በመተባበር ሠርተውታል። ከኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር በተገኘው መረጃ መሠረትም ወደ 17 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል።
በአሥተዳደሩ የደብረ ብርሃን እና አካባቢው ፕሮጀክት ማናጅመንት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ንጋቱ ውድነህ ለአሚኮ እንደገለጹት ለድልድይ ተሸካሚ ምሶሶ መትከያ ቦታ ወንዙን የማድረቅ ሥራ በእጅጉ አስቸጋሪ ነበር። በሂደቱ 10 ፓምፕ መቃጠሉንም በማሳያነት አንስተዋል። የተዘጋጀው አማራጭ መተላለፊያ ተደጋጋሚ ብልሽት እያስተናገደ መንገደኞችን ማጉላላቱም ሌላኛው ችግር ነበር ተብሏል።
ሆኖም ግን የውኃውን የፍሰት አቅጣጫ በመቀየርና የብረት ተሸካሚ ምሶሶዎችን በማጠናከር በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የተደረገው ጥረት ስኬታማ መኾኑን አመላክተዋል። እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ያለውን ሃብት በአግባቡ ከመጠቀም ባለፈም የአሥደዳደሩ የሳይት መሀንዲሶች በቦታው በመኾን ሙያዊ ድጋፍና ክትትል አድርገዋል።
ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ ድልድዩ መደበኛ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ መጀመሩን ኢንጅነር ንጋቱ አስታውቀዋል። የአካባቢው ማኀበረሰብ ለነበረው ትግስትም ምስጋና አቅርበዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን መንገድ መምሪያ ኀላፊ ሳሳሁ ጌታ ድልድዩ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው መኾኑን ገልጸዋል። በተለይ በክረምቱ ሊከሰት የሚችልን የትራንስፖርት አገልግሎት መስተጓጎል በአስተማኝ ኹኔታ ያስቀራል ብለዋል፡፡ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችን ያለምንም ችግር ወደ ዩኒቨርስቲ ለማጓጓዝ መድረሱም ትልቅ ስኬት መኾኑንም አስረድተዋል።
የብረት ድልድዩ በአንድ ጊዜ አንድ ተሽከርካሪን ብቻ ማሳለፍ የሚችል በመኾኑ አሽከርካሪዎች በጥንቃቄ ሊጠቀሙ እንደሚገባም መልእክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!