“ምንም ድሃ ብኾን የማቀርበው ባጣ

45

እንግዳ እወዳለሁ ከወሎ፣ ከሽዋ፣ ከጎጃም የመጣ” ወልቃይቴዎች

ሁመራ: ሐምሌ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በቋንቋ መግባባት፣ በባሕል መገለጥ፣ በወግ መነጋገር፣ በእሴት መከባበር፣ በልማድ መገራት እና በማንነት መኩራት ምን ዓይነት የተለየ የደስታ ስሜት እንዳለው ለማየት እንደ እኔ ወልቃይት ደጀና ላይ መከሰትን ሳይጠይቅ አይቀርም፡፡ እንኳን ልጆቻቸው ጥጆቻቸው እንኳን በደስታ ብዛት ይቦርቃሉ፤ በግርምት ይመለከታሉ፡፡ “ምድር ቁሊጥ ኾናለች” ይላሉ እንዲህ ዓይነት የፍቅር ትዕይንትን እና ኹነትን የሚታደሙ የሀገሬው ሰዎች፡፡

ሴቶቹ ከብዙ የመከራ ዘመናት በኋላ የእናትነት ወጉ ደርሷቸው ሽር ጉድ ይላሉ፡፡ ወንዶቹ የማያልፉ የሚመስሉ እነዚያን የግፍ ዘመናት በጽናት እና በጀግንነት አሳልፈው አንጻራዊ ሠላም ስላገኙ የአባወራነትን ጣዕም የሚያጣጥሙ ይመስላሉ፡፡ አዛውንቶቹ ያለፈውን በትዝብት፣ የአሁኑን በስሜት እና መጻዒውን በስስት እየናፈቁ ዓይኖቻቸው የደስታ እምባ ጤዛ አዝለው አስፈሪ ዝምታ ይስተዋልባቸዋል፡፡ ሽማግሌዎቹ አንደበታቸው ባይከፈት እንኳ ዝምታቸው ግን ብዙ ይናገራል፡፡

ታዳጊዎቹ ትናንት ይከለከሉ የነበሩትን የባሕል እና የማንነት መገለጫዎች ዛሬ በነጻነት ሲከወኑ ማየታቸው ግርምት ሳያጭርባቸው አልቀረም፡፡ ወጣቶቹ እና ልጃገረዶቹ የዚህ ትዕይንት አድራጊ ፈጣሪ ኾነው ላየ “እድለኞች ናችሁ! ምክንያቱም ትናንትና በእናንተ እድሜ፤ በዚች ቀየ ይህንን ደስታ እንዳያዩ የተከለከሉ ስንቶች ነበሩ” ያሰኛል፡፡ የማይነጋ ሌሊት፤ የማያልፍ ማዕት የለምና ያንን የጨለማ ዘመን በብርታት አሳልፈው ዛሬ ላይ እንዲህ ለመሰባሰብ በቅተዋል፡፡

ነጭ ለባሾቹ ወልቃይቴዎች ከነባርኔጣቸው አስተውሎ ለተመለከታቸው አካባቢውን የበረዶ ክምር አስመስለውታል፡፡ የእናቶቹ ውበት “ፈጣሪ ታጥቦ ሰርቷቸዋል” የሚባልላቸው አይነት ናቸው፡፡ የወልቃይት ሴቶችን ውበት ለመግለጽ ቃል ያጥራል፡፡ “የምትበላው ስጋ የምትጠጣው ጠጅ፤ ታዲያ ምን ያደርጋል አማራ ኾነች” ነው ያሉት፤ ነገሩ እንደዚያ ነው፡፡

በአንድ ዳስ ጥላ ጥግ ሁለት ምድጃ ይስተናገዳል፡፡ አንዱ የክርስቲያኖቹ ሌላኛው ደግሞ የሙስሊሞቹ ነው፡፡ ወጥ እንጨት እና ቢላ ሲጋሩ አላየንም እንጅ ፍቅር አቀራርቦ ሲያሳስቃቸው እና ሲያስተቃቅፋቸው ተመልክተናል፡፡ ማዕዱን በምስጋና የሚባርኩት ቀሳውስት፤ ከማዕድ በኋላ ለምስጋና ሶላት የተንበረከኩት ሼኮች ምድራዊውን ማዕድ ሰማያዊ ጸጋ እና በረከት አብዝተውበታል፡፡ ፍቅር የማይገዛው ምድራዊ ነገር እንደሌለ ደጀናዎች በቂ ምስክር ናቸው፡፡

የአካባቢው አድባር ከኾነው ታላቅ ዋርካ ሥር ፈረስ የሚያስጋልብ ዳስ ተጥሏል፡፡ ገንቦ ተዘንብሎ፣ ሞሰብ አረግርጎ ይቀርባል፡፡ ሥጋ እንደ ጎመን ሲከተፍ አፌን ከፍቼ እያየሁ ተመስጫለሁ፡፡
“ጠጅ አማረው ልቤን ጠላን ሆዴ ናቀው፤

ይህንን ቢሰማ ውኃ እንዴት ይደንቀው” እንዳለ የጎንደር አዝማሪ ጠጅ እና ጠላ ግራ እና ቀኝ ተዘንብለው ይንቆረቆራሉ፡፡ አንኮላ ሙሉ ጠላ፤ ብርሌ ሙሉ ጠጅ እንዳሻ ተመርጦ ይጠጣል፡፡ ለዛ ያለው ጨዋታ፣ ደርዝ ያለው ንግግር እና ፍሬ ያለው ቁም ነገር ከቀኝ ከግራ፤ ከፊት ከኋላ ይደመጣል፡፡
በጸሎት ተጀምሮ በምስጋና የተጠናቀቀው ማዕድ ከፍ ካለ በኋላ ዳሱ ለሞቀ ጨዋታ ዝግጁ ኾኗል፡፡ ታሪክ አዋቂው ዓለም አጫዋች ማሲንቆውን አፈራርቆ እየቃኘ መንፈሳችንን በስሜት እና በሃሴ እንደ ማዕበል መናጥ ጀምሯል፡፡ ጎንደርኛ ቅኝት የጎላበት እና ከውጭ በልጃገረዶች የሚደበደበው የከበሮ ድምጽ ልባችንን አሸፍቶታል፡፡ የተስረቀረቀ የሀገር ቤት ድምጽ ያዘለው ጨዋታ ቀልብን የመግዛት ተፈጥሯዊ ምትሃት አለው፡፡ ዙሪያ ገባውን የሚስተዋለው የደስታ ስሜት እድሜ ይጨምራል፡፡

ጨዋታው ደርቷል፤ ዳሱ በሰው ሞልቷል፡፡ ፉከራ እና ሽለላ፤ እስክስታ እና ዜማ ፍጹም የበላይነትን ወስደዋል፡፡ በእያንዳንዱ ዘፈን እና ፉከራ፤ ቀረርቶ እና ሽለላ ውስጥ አጥንት ሰርስረው የሚገቡ በሳል መልዕክቶችን ማዳመጥ የተለመደ ነው፡፡ ወገባቸው ብቻ ሳይኾን አማርኛቸውም በቅኔ ይሽከረከራል፡፡

ትናንትና ማታ በቀደም በህልሜ፤
እርካቤ ተሰብሮ ከባሕር ላይ ቆሜ፡፡
እርካቤም አንተ ነህ ውኃውም እምባየ፤

እንደ ተለያየን ቀረን ወይ ጀግናየ፡፡ ሲሉ ለነጻነታቸው እና ለማንነታቸው አንገት ለአንገት ተናንቀው ያለፉትን ሁሉ ያስታውሷቸዋል፡፡ የዛሬዋ ቀን ትመጣ ዘንድ ላለፉት አራት አስርት ዓመታት በርካቶች ውድ የኾነውን የሕይዎት ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ምንም እንኳን ደስታ ላይ ቢኾኑም ወልቃይቴዎች የተከፈለላቸውን ውድ ዋጋ ግን ፈጽሞ አይዘነጉም፡፡ በዚያ የደስታ ቆይታ ውስጥ ይህን መሰሉ ስሜት አብዝቶ ይረብሻል፡፡

ወልቃይቴዎች ጀግንነት ብቻ ሳይኾን ጨዋታም ያውቃሉ፡፡ ቀልዳቸው እንደ ተኩሳቸው አንጀት አርስ ነው፡፡ ተኩሰው ካንገት በላይ ካልመቱ የሚበሳጩት በጌምድሬዎች ተጫውተውም ከጭንቅላት የማይጠፋ ትዝታን ያስቀራሉ፡፡ በጨዋታ ማመስገን በሽለላ ማጀገን፤ በፉከራ ማደርጀት በቀረርቶ ማደራጀት ይችላሉ፡፡ በዳሱ ውስጥ ከተሰባሰብነው እንግዶች መካከል የተወሰነው እንግዶች “ጸጉረ-ልውጥ” መኾናችንን ያስተዋለው ዓለም አጫዋች፡-

“ምንም ድሃ ብኾን የማቀርበው ባጣ

እንግዳ እወዳለሁ ከወሎ፣ ከሽዋ፣ ከጎጃም የመጣ” ሲል ተቀኘብን፡፡ በዚህ ዳስ ውስጥ ከነበረው ያላወጋኋችሁ ብዙ ነገር አለ፤ እመለሳለሁ፡፡

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዳንሻ በራስ አቅም የመልማት ተምሳሌት እና አርዓያ ናት” ከንቲባ አብዱለሀብ ማሙ
Next articleለክረምት የግብርና ልማት ሥራዎች ትኩረት መሥጠት እንደሚገባ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዱ ሁሴን አሳሰቡ።