“ዳንሻ በራስ አቅም የመልማት ተምሳሌት እና አርዓያ ናት” ከንቲባ አብዱለሀብ ማሙ

33

ሁመራ: ሐምሌ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከ29 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ ያሰገነባቸውን የመሰረተ ልማት ሥራዎች አጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃቱን የዳንሻ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል፡፡

በረኽኛውን ከደገኛው የምታገናኝ ድልድይ እና ደረቅ ወደብ የኾነች ከተማ ናት፤ ዳንሻ ከተማ አሥተዳደር፡፡ ትርፍ አምራች የሆኑት የጠገዴ እና ወልቃይት፤ የባዕከር እና ሰቲት በርሃማ አካባቢዎች በዙሪያዋ የሚገኙት ዳንሻ ትልቅ የመልማት አቅም ያላት ከተማ ብትኾንም መጠቀም እንዳትችል ተደርጋ ቆይታለች፡፡

ከጎንደር እስከ ኦማህጀር፣ ከአብርሃ ጅራ እስከ ሁመራ፣ ከባህር ዳር እስከ ባዕከር መገናኛ ማዕከል ሆና የተመሰረተችው ዳንሻ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በመሪ ማዘጋጃ ቤት መዋቀሯ እድገቷን እንደ ካሮት ቁልቁል አድርጎት ቆይቷል ይላሉ ነዋሪዎቿ፡፡ በቅርቡ ራሷን የቻለች እና በከተማ አሥተዳደር የምትመራ ከተማ በመኾኗ ቁጭት ያዘለውን የዘመናት ብሶት ለማካካስ ቀን ከሌሊት እየተሰራ ነው ይላሉ፡፡

በአራት ቀበሌዎች የተዋቀረችው የዳንሻ ከተማ አስተዳደር ከ30 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች መኖሪያ ናት ያሉን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አብዱለሀብ ማሙ ናቸው፡፡ ዳንሻ በከተማ አስተዳደር መዋቀር ከነበረባት ጊዜ እጅግ ዘግይታለች የሚሉት ከንቲባው ወያኔ ተጠቅሞባቸው ካለፉ የአማራ ክልል ነባር ርስቶች መካከል አንዷ እና ግንባር ቀደሟ ከተማ ናት ይላሉ፡፡ ባለፉት የጭቆና ጊዜያት በርካታ ሰፋሪዎች ከሌሎች አካባቢዎች መጥተው በከተማ አስተዳደሩ ዙሪያ እንዲሰፍሩ ተደርጎ ነበር የሚሉት ከንቲባው አልምተው ያገኙትን መዋዕለ ንዋይ የሚያፈስሱት ግን ተከዜ ባሻገር ነበር ብለዋል፡፡

የዳንሻ ከተማ አስተዳደር ሕዝብ የዘመናት ጥያቄ ነጻነት እና ማንነቴ ይከበር የሚል ነበር የሚሉት ከንቲባ አብዱለሀብ የሕዝቡ ጥያቄ በኃይል ተመልሶ ነጻነታቸውን ካገኙ ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል ብለዋል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ያለምንም የመንግሥት በጀት ትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና እና መሠል አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አገልግሎት ሰጥተዋል፤ ይህም የሕዝቡን ጥንካሬ እና ነጻነት ወዳድነት የሚያመላክት ነበር ነው ያሉት፡፡

የሕዝቡን ጊዜያዊ ነጻነት ዘላቂ ለማድረግ ከመሥራት ባሻገር የሕዝቡን የዘመናት የመልማት ጥያቄ መመለስ የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ተግባር ነበር ያሉት ከንቲባው ከሕዝቡ፣ ከአጋር አካላት እና ከአካባቢው ተወላጆች ጋር በመሆን በአጭር ጊዜ ረጂም ርቀት መጓዝ ችለናል ነው ያሉት፡፡
“ዳንሻ በራስ አቅም የመልማት ተምሳሌት እና አርዓያ ናት” ያሉት ከንቲባ አብዱለሀብ ማሙ መንግሥት ሕዝቡ ያነሳቸውን መሠረታዊ ጥያቄዎች ሊመልስ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የዳንሻ ከተማ አስተዳደር ሕዝብ ለዘመናት በዘለቀው ጥንካሬው እና በወንድሞቹ መራር ተጋድሎ ያስከበረውን ማንነት ለድርድር የሚያቀርብበት ታሪካዊ ስህተት ዳግም አይሰራም ያሉት ከንቲባው የተጠየቀውን ሕጋዊ የማንነት ጥያቄ መመለስ ወቅቱ የሚጠይቀው የቤት ሥራ ነው ብለዋል፡፡ ሌላው በዚህ ዘመን ሦስት ዓመታትን ያለ መንግሥት በጀት ራስን በራስ እያስተዳደሩ መዝለቅ ከጀርባው መራር ሃቅ ስለመኖሩ የሚያረጋግጥ በመሆኑ የሚመለከተው ሁሉ የሕዝብን መሠረታዊ ችግር ማዳመጥ እና መመለስ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ባለፉት ሦስት የነጻነት ዓመታት ከሕዝቡ ጎን ለነበሩ፣ ውድ የሕይዎት እና የሃብት ዋጋ ለከፈሉ ሁሉ ዳንሻ በእጅጉ ታመሰግናለች ያሉት ከንቲባው ከጦርነት እስከ ልማት ከጎናችን የዘለቀው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ምዕራብ እዝን በሕዝቡ እና በከተማ አሥተዳደሩ ስም እንደሚያመሰግኑ ገልጸዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ከሕዝብ፣ ከውስጥ ገቢ እና ከአጋር አካላት ባገኘው 29 ሚሊየን 727 ሺህ ብር ያስገነባቸውን የመሠረተ ልማት ሥራዎች ያስመርቃል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ምክር ቤት የክልሉን በጀት ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትን የ2016 ዓ.ም በጀት መርምሮ አጸደቀ።
Next article“ምንም ድሃ ብኾን የማቀርበው ባጣ