
ባሕር ዳር: ሐምሌ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የቁልቢ ገብርኤል ክብረ-በዓል በሰላም እንዲከበር የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል በቂ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ግብረ ኃይሉ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ሜታ ወረዳ ሐምሌ 19 ቀን 2015 ዓ.ም የሚከበረው የቁሉቢ ገብርኤል ክብረ-በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታ አካላት ዝግጅት አድርገው ወደ ተግባር መግባታቸውን ገልጿል።
የጋራ ግብረ-ኃይሉ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ እና በምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች ሰላምና ደህንነት እያስከበረ መቆየቱንና አሁን ላይ የአካባቢው ሰላም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።
በአካባቢው የፀጥታውን ሁኔታ የበለጠ ለማጠናከር በሁሉም አቅጣጫ አስፈላጊውን ጥበቃና ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኝ በመግለጫው አመላክቷል፡፡
በበዓሉ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አሸከርካሪዎች የትራፊክ ሕግን አክብረው በማሽከርከር የበዓሉ ታዳሚዎች ያለ ምንም የትራፊክ አደጋ በዓሉን በሰላም አክብረው እንዲመልሱ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የጋራ ግብረ-ኃይሉ አሳስቧል።
በመጨረሻም የአካባቢው ኅብረተሰብ ለእንግዶቹ ቅድሚያ በመስጠት የቆየ የእንግዳ ተቀባይነት ባሕሉን እያሳየ አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ እና ለሰላምና ደኅንነት ስጋት የሆኑ ነገሮችን ሲመለከት በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች ጥቆማ በመስጠት የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ የጋራ ግብረ-ኃይሉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!