
ባሕር ዳር: ሐምሌ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዞኑ አራት ወረዳዎች ባለፈው ወራት የተከሰተውን የኩፍኝ በሽታ መቆጣጠር መቻሉን የዞን ጤና መምሪያ አስታውቋል።
የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ ሲስተር ፈለቁ መኮንን በዞኑ በሚገኙ አራት ወረዳዎች ላይ የኩፍኝ በሽታ ተከስቶ እንደነበር ተናግረው ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ድርጅት በነጻ በተገኘ የክትባትና የህክምና መድሃኒት በሽታውን መቆጣጠር ተችሏል ብለዋል።
በሽታው በዞኑ ራያ ቆቦና ቡግና ወረዳዎች የከፋ በመሆኑ በዘመቻ መልክ ለመስራት መገደዳቸውን ጠቅሰው ፤ በራያ ቆቦ ስድስት ህጻናት ሕይወታቸው ሲያልፍ እንደ ዞን 103 ሺ 320 ለሚኾኑ ሰዎች የህክምናና ክትባት መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡
ግዳን፣ ራያ ቆቦ፣ ቡግና ወረዳዎችና ቆቦ ከተማ በርካታ ህፃናት በበሽታው ተይዘው በአጭር ጊዜ ህክምና ተሰጥቷቸው ፈውስ አግኝተዋል ብለዋል።
ለኩፍኝ በሽታው መነሳት ዋናው ምክንያት ባለፉት ሁለት ዓመታት በጦርነት ምክንያት በእነዚህ አካባቢዎች ክትባት ባለመሰጠቱ መሆኑን የገለጹት ኃላፊዋ በጦርነቱ በርካታ ጤና ኬላዎች በመዘረፉ የማቀዝቀዣ መሣሪያ የላቸውም ብለዋል።
በጤና ኬላዎች የክትባት መድሃኒት ማስቀመጥ ባለመቻሉ ኅብረተሰቡ በአቅራቢው ከሚገኙ ጤና ጣቢያዎች ድረስ በመሄድ ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡ አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!