የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማቶችን ከማሟላት በዘለለ በግብዓት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡

514

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 14/2012ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዙሪያ ከአጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡ ትናንት ታኅሣሥ 13/2012 ዓ.ም በባሕር ዳር በተደረገው ውይይት በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ከተማ አስተዳደር እየተገነባ ያለውን የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና በደቡብ ምዕራብ አማራ በግንባታ ላይ ባሉት ሰባት የገጠር ሽግግር ማዕከላት የግንባታ አፈጻጸም እና ቀጣይ መከናወን የሚገባቸው ተግባራት ላይ መክሯል፡፡

የክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ደሴ አሰሜ ባቀረቡት የውይይት መነሻ የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ የግንባታ አፈጻጸም 80 በመቶ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡ በተያዘው ዓመት ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ደሴ ንግግር አራት ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኩ ቦታ ተረክበው ግንባታ እያከናወኑ ይገኛሉ፤ ግንባታው የተጠናቀቀው የዘይት ፋብሪካ በመጪው ጥር ሥራ ይጀምራል፡፡ በተጨማሪም 10 ባለሀብቶች በእንስሳትና እንስሳት ተዋጽኦ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በጥራጥሬና ቅባት እህሎች ለመሠማራት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ለግብርና ምርት ደረጃ በማውጣት፣ በማጣራት፣ ደረጃ በመስጠትና በማሸግ ለኢንዱስትሪዎች የሚያቀርቡ ሰባት የገጠር ሽግግር ማዕከላት እየተገነቡ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ በሞጣ እየተገነባ ያለው ማዕከል 85 በመቶ መድረሱንና በተያዘው ዓመት እንደሚጠናቀቅም ተናግረዋል፡፡
የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ቢሆንም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አሁንም ስጋት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የኃይል አቅርቦቱ መሟላት የነበረበት የፓርኩ ግንባታ ሲጀመር ቢሆንም የፌዴራል መንግሥት ምንም አለመሥራቱ ነው የተነገረው፡፡ ሰብስቴሽን እንዲገነባና መስመር እንዲዘረጋ የክልሉ መንግሥት በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረቡና የተሰጠ ምላሽ አለመኖሩ ነው የተነገረው፡፡

በውይይቱ ተሳታፊዎች በስፋት የተነሳው ስጋት ደግሞ የግብዓት እጥረት ነው፡፡ ኢንዱስት ፓርኩ ወደ ሥራ ሲገባ በዓመት 824 ሺህ 476 ሜትሪክ ቶን የግብርና ምርቶችን ይጠቀማል፡፡ በዚህ ጊዜ ባለው ምርት ፍላጎቱን ማሟላት እንደማይቻል በማንሳትም የግብርና ተቋሙ እና የምርምር ማዕከላት ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚገባቸው አስተያዬት ተሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደረጃ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ መላኩ አለበል በቂ ግብዓት መኖሩ በጥናት መረጋገጡን ገልጸዋል፡፡ ጥናቱ ከተሠራ በኋላ ግን በምርት ጥራት፣ ለባለሀብት በሚቀርብበት መንገድ እና ሌሎች ተግባራት ላይም ትኩረት ሰጥቶ ያለመሥራት ችግር መኖሩን ነው አቶ መላኩ የተናገሩት፡፡ መሠረተ ልማት ከማሟላት በዘለለ የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ በሚፈልጉ በርካታ ተግባራት ላይ ተረባርቦ መሥራት ተገቢ እንደሚሆንም አሳስበዋል፡፡ ፓርኩን በተሟላ መልኩ ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጥ አጋርና ባለድርሻ አካላት ትርጉም ያለው ሁሉን አቀፍ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባም አቶ መላኩ አሳስበዋል፡፡

የቡሬ የተቀናጀ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ከመጀመሩም አስቀድሞ በቡሬ፣ ፍኖተ ሠላምና አካባቢ ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት ችግር መኖሩንና የአካባቢው አስተዳደር ለ‹ሰብስቴሽን› ግንባታ የሚውል ቦታ አዘጋጅቶ እየጠበቀ እንደሚገኝ አብመድ በተደጋጋሚ ዘግቧል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous article‹‹ሕጋዊ መሆን አለመሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት የተማሪዎችና ተቋማት ነው፡፡›› የከፍተኛ ትምህርት አግባብነት እና ጥራት ኤጄንሲ
Next articleቺርቤዋ-30-2-2012