
ሁመራ: ሐምሌ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዕድሜያቸው 90 ሊገባ ጥቂት የሚባሉ ዓመታት ቀርቷቸው እንኳን ፈረስ ጭነው ይጋልባሉ፡፡ የወጣትነት ዘመን ወኔያቸው ተፈጥሯዊ በኾነው ሽምግልና የበረደ አይመስልም፡፡ በጫዋታዎቻቸው መካከል “የኢትዮጵያ አምላክ” የሚለው ንግግራቸው ቀልብ የመግዛትን ምትሃታዊ ኃይል ተላብሷል፡፡ ሰው አቅርበው ሲያላምዱ እና ሲያጫውቱ እንግድነትን ያስረሳሉ፡፡ እንኳን የሀገሬው ሰው “ባላምባራስ ይርዳው” የሚል ስያሜን የቸሩት ፈረሳቸው እንኳን ድምጻቸውን ይሰማል፡፡ ፈረስ እወዳለሁ ብለውኛል፤ በልጅነታቸው ጎበዝ ፈረስ ጋላቢ እንደነበሩም አጫውተውኛል፡፡
ጠገዴ እትብታቸው የተቀበረባት ምድር ብቻ ሳትኾን ብዙ ውጣ ውረዶችን ያዩባት አካባቢ በመኾኗ እጅግ አብዝተው ይወዷታል፡፡ ጠገዴን ሲያነሱ “ጠገዴ የበለው ሀገር፤ ግብሩ ጦር፤ ጦሩ ዘገር፤ ሰልፉ በቀኝ” ሲሉ ይቀኙላታል፡፡ ባለፈው ጊዜ ክፉ ዘመን ገጥሞት የመከራ ጊዜን አሳልፏል የሚሉት ጠገዴ የመከራው ተጋሪ፣ የፈተናው ተካፋይ እና የክፉ ዘመኑ ተቋዳሽ ከኾኑት ታላላቅ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው፤ ሻምበል አዳነ ታፈረ፡፡ በዘመነ ወያኔ ከእስር እና ዝርፊያ የተረፈው ሕይዎታቸው ሚስጥር የፈጣሪ ተዓምር ነው ይላሉ፡፡ በአካል ተገናኝተን አይረሴ እና መልካም ጨዋታን ተጨዋወትን፡፡
ገና ከመነሻው የታላቋ ትግራይ ሪፐብሊክን ለመመስረት ወደ በርሃ የወረደው የህወሐት ቡድን ሀገር ለመኾን ለም መሬት እና ወደ ውጭ የሚያገናኝ ድንበር እንደሚያስፈልግ ተረድቷል፡፡ ምኞቱን እውን ለማድረግ ይችል ዘንድም ከትግራይ ነባር ይዞታዎች ውጭ የሀገር ውስጥ ወረራ በማካሄድ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ድንበር የኾነውን የተከዜ ወንዝን በመሻገር በ1970ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ እስከ 1984 ዓ.ም አካባቢ ድረስ ወልቃይትን፣ ጠለምትን፣ ጠገዴን እና አካባቢውን በኃይል ተቆጣጠረ፡፡
ወራሪው ኃይል ወሎ ሲያደር እግረ መንገዱን ሀገር የመምራት እድል ማግኘቱን ተከትሎ በምዕራብ አቅጣጫ የራያ አላማጣ፣ የኮረም እና የኦፍላ አካባቢዎችን በመውረር ከተመቸን እንቆያለን፤ ካልተመቸን ታላቋን ትግራይ እንመሰርታለን የሚል የልብ ልብ ተሰማቸው፡፡ በተወረሩ አካባቢዎች የሚኖረው ሕዝብ ማንነቱ አማራ ሲኾን በኃይል የተወረሩት አካባቢዎች ደግሞ የጎንደር (በጌምድር) እና የወሎ አካል ኾነው ለዘመናት የዘለቁ የአማራ ነባር እርስቶች ለመኾናቸው ዋቢዎች ብዙ ናቸው፡፡
ሁሉም በወረራ የተያዙ አካባቢዎች በታሪክ ትግራይ የኾኑበት አጋጣሚ ፈጽሞ እንዳልተፈጠረ ይታወቃል፡፡ ህወሐት የትጥቅ ትግል ሲጀምር 1968 ዓ.ም አካባቢ የትግል ስልት ብሎ የነደፈው ፍኖተ ካርታ (ማኒፌስቶ) አማራ ጠል ትርክቶችን መዝራት ነበር፡፡ ለትግል ዓላማው አንዱ ማስፈጸሚያ ስልት ደግሞ የፈጠረውን ጸረ-አማራ ትርክት በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉ በማስረጽ አማራ በሌሎች ብሔሮች እና ብሔረሰቦች፤ አልፎ አልፎም በራሱ በአማራ ልጆች ዘንድ በጥርጣሬ እንዲታይ ማድረግ ነበር፡፡
መንበረ ሥልጣኑን ከደርግ እጅ ነጥቆ ሀገር መምራት የጀመረው ህወሐት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ሕዝባዊ እምቢተኝነት ሲበዛበት ሞጋች የሚላቸውን የኀብረተሰብ ክፍሎች እየነጠለ ማጥቃቱን ቀጠለበት፡፡ በማኒፌስቶው የትግራይ ሕዝብ ብሔራዊ ትግል ዓላማው ጸረ-አማራ ብሔራዊ ጭቆና፣ ጸረ-ኢምፔሪያሊዝም እና ጸረ-ንዑስ ከበርቴአዊ ጠጋኝ ለውጥ ነው ያለው ህውሐት ለዓላማው መሳካት ታላላቅ ሰዎችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ ታሪክ አዋቂዎችን እና የሀገር አውራ የሚላቸውን መርጦ ማስወገድ ምርጫው አደረገ፡፡
የታሪክ፣ የመንግሥት አሥተዳደር፣ የባሕል፣ የሃይማኖት እና የትውፊት ሙዚየም የኾኑ ታላላቅ የአማራ ተወላጆች የህወሐት ማኒፌስቶ ማስፈጸሚያ ሰለባ ኾኑ፡፡ በህወሐት እጅ የስቃይ ቀንበርን ተሸክመው ካሳለፉ በርካታ ታላላቅ ሰዎች መካከል የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት እና ራያ አማራዎች ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የወያኔ የተንኮል ጥግ ሀገርን እና ሕዝብን ታላቅ በኾነ የውትድርና ሙያ ያገለገለ ሠራዊትን “የደርግ ወታደር” የሚል ስያሜ ሰጥቶ ውድ የኾነውን ሙያ ዝቅ አደረገው ያሉን በጠገዴ ወረዳ ምድረ ገበታ ቀበሌ ያገኘናቸው የ88 ዓመት አዛውንቱ ሻምበል አዳነ ታፈረ ነበሩ፡፡
የወያኔ ድፍረት እና ንቀት ከደርግም ያልፋል የሚሉት ሻምበል አዳነ ታሪክ ሲጠቅሱ ቢትወደድ አዳነ መኮንን የመሩት አውራጃ፤ ከፊታውራሪ አዲሱ መኮነን እስከ አዝማች ይርጋ ነጋሽ፣ ከፊታውራሪ ደምስ አስፋው እስከ ፊታውራሪ በሪሁን ደሴ እና በነፊታውራሪ ተሾመ ጎበዜ የተመራው ጠገዴ ባልታሰበ ጊዜ በወያኔ እጅ ወደቀ ሲሉ ይቆጫሉ፡፡ በርካቶቹ ታላላቅ ሰዎች የጠገዴን ወደ ትግራይ መካለል እስከ ሕይዎት ፍጻሜያቸው ተቃውመዋል፤ ነገር ግን ወልቃይት፣ ጠገዴ እና ጠለምት አልተደራጀም ነበርና ተበልቶ ባጀ ይላሉ ሻምበል አዳነ፡፡
ጠገዴ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ በርካቶቹ ባለርስቶቿ በወያኔ ሴራ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ጠገዴ ተወላጆቿ ከሌላ ቦታ መጥተው ባለርስት ከኾኑ ሰፋሪዎች የእርሻ መሬት የተከራዩባት ወረዳ ኾና ነበር የሚሉት ሻምበል አዳነ እርሳቸውም መሬታቸውን ተነጥቀው፣ መሳሪያቸውን ተቀምተው እና ከቦታ ቦታ ተንከራትተው የፈተና ጊዜያትን አሳልፈዋል፡፡ የወያኔ ዓላማው አማራን ማቆርቆዝ እና ትግራይን በወረራ መሬት ደርዝ ማስያዝ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ወያኔ ከእኔ ጋር የነበረው ግጭት የሚጀምረው ጠገዴ የትግራይ መሬት መኾኑን እመን እና ትግሪኛ ቋንቋን መናገር አለብህ የሚል ሲኾን ከአያት ቅድመ አያቴ የሰማሁትም ኾነ ያየሁት ጠገዴ ሥሩ ጎንደር ፣ ምክሩ ከበጌምድር እንደነበር ነው ይላሉ፡፡ ትግርኛ ቋንቋን ተናገር ሲባሉም “ያለአባቴ” የሚል ምላሽ የሚሰጡት ሻምበል አዳነ ከወያኔ ጋር እሳት እና ጭድ ኾነው ቆይተዋል፡፡ በአማርኛ ማልቀስ ወንጀል፣ በአማርኛ ደስታን መግለጽ ነውር፣ በባሕል ማጌጥ የሚያሸማቅቅ እና ማንነትን መጠየቅ የሚያስጠይቅ ነበር ነው ያሉት፡፡
በህወሐት ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያ ከሚለው መጠሪያ ይልቅ መንደር እና ሰፈር ላይ መቀርቀር ይበዛ ነበር፤ ይህ ደግሞ ትንሽ መኾንን የሚያመላክት ነው፡፡ ላለፈው ሥርዓት ከኢትዮጵያ ይልቅ ትግራይ ትበልጣለች የሚሉት ሻምበል አዳነ “ወያኔ ታላቅ ሀገርም ኾነ ታላቅ ሰው አይወድም ነበር፤” መሠረታዊ ህመሙም ከዚህ ትንሽነት የሚመነጭ ይመስለኛል ነበር ያሉት፡፡
ከሕዝብ ሆድ የወጣ መንግሥት እና ከውኃ የወጣ ዓሣ ሁለቱ አንድ ናቸው የሚሉት አዛውንቱ ሻምበል ካለፈው መማር፣ አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እና በልዩነቶች ላይ ጊዜ ወስዶ መነጋገር እንደሚጠቅም ይመክራሉ፡፡ አባቶቻችን ብልህ መሪዎች ነበሩ፤ እንኳን ታላላቆችን እረኞችን ያደምጡ ነበርና ጥበብን ከቀደሙት መቅዳት ሀገር ለመምራት አያሳፍርም ይላሉ፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!