
ባሕር ዳር: ሐምሌ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር ፣2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣6ኛ መደበኛ ጉባኤ በሦስተኛ ቀን ውሎው የክልሉን የ2016 ዓ.ም በጀት መርምሮ አጽድቋል።
ርእሰ መሥተዳደሩ ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) እንደገለጹት የቀረበው የ2016 ዓ.ም በጀት የ2015 ዓ.ም በጀትን መነሻ ያደረገ ነው። የተመደበው የ2016 ዓ.ም በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውልም አሳስበዋል።በጀት በፍትሐዊነት መመደብ መሰረታዊ ጉዳይ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳደሩ የተመደበውን በጀት በአግባቡ እና በቁጠባ በመጠቀም ለታለመለት ዓላማ ማዋል ከሁሉም አካላት የሚጠበቅ ነው ብለዋል።
በተያያዘም ርእሰ መሥተዳደሩ የውስጥ ገቢ መሰብሰብ ሥራ ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ነው ብለዋል። በበጀት ዓመቱ ከጠቅላላው የ2016 ዓ.ም በጀት የልማት ፋይናስ ውስጥ 89 ቢሊዮን 279 ሚሊዮን 467 ሺህ ብር በክልሉ ገቢ የሚሰበሰብ ኾኖ ጸድቋል። በጀታችን ከፍ እንዲል ለማድረግ ገቢ አሰባሰብ ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
ክልሉ ገቢ የመሰብሰብ ዕቅዱን እንዲያሳካም ለሰላም ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል ነው ያሉት። ክልሉ ገቢ መሰብሰብ ላይ መዋቅራዊ ለውጥ ላይ መኾኑን የገለጹት ርእሰ መሥተዳድሩ የኢኮኖሚ ማእከል የኾኑ ከተሞች ላይ የገቢ መሰብሰብ ሥራው በትኩረት መሠራት አለበት ብለዋል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!