
ባሕር ዳር: ሐምሌ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) በ2015 በጀት ዓመት በ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክት ትግበራ ከ7 ሺህ በላይ የመማሪያ ክፍልችን ማስገንባቱን ገልጿል፡፡
አልማ ከተመሠረተ ጀምሮ በክልሉ የተለያዩ ልማት ሥራዎችን በተለይም ደግሞ በትምህርት፣ በጤናና በሥራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ የገለጹት የአልማ የሕዝብ ግንኙነት እና ተግባቦት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ሞገስ ናቸው። ማኅበሩ በ2015 በጀት ዓመት “ማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክት ትግበራ” ማስፈጸሚያ ስልትን በክልሉ በመተግበር 7 ሺህ 328 የመማሪያ ክፍሎችን በማጠናቀቅ ለ2016 የትምህርት ዘመን ክፍት እንደሚኾኑ ተገልጿል።
በማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክት ትግበራ በክልሉ የሚሠሩ መማሪያ ክፍሎችን ማኅበረሰቡ በራሱ ጉልበትና ገንዘብ እንዲያከናውናቸው የሚሠራበት ፕሮጀክት መኾኑን አቶ አለማየሁ ገልጸዋል፡፡
አሠራሩም ማኅበረሰቡ በፕሮጀክቶች ላይ የእኔነት ስሜት እንዲኖረው፣ ፕሮጀክቶች ወጭ ቆጣቢ በኾነ መንገድ፣ በጥራት እና በተቀመጠላቸው ጊዜ ተጠናቅቀው አገልግሎት እንዲሠጡ የማድረግ አቅም ፈጥሯል፡፡ የፕሮጀክት አፈጻጸም ግልጸኝነትንም በማኅበረሰቡ ዘንድ ፈጥሯል፡፡ ማኅበረሰቡ ራሱን በራስ የማልማት አቅም እንዲያዳብር አድርጓልም ብለዋል፡፡
የትግበራ ስልቱን ሌሎች ልማት ሥራዎችን ለማስፈጸም ዋነኛ ስልት ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክት ትግበራ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሦሥት ዓመታት በደቡብ ጎንደርና በሰሜን ሸዋ ዞኖች በሙከራ ሲተገበር ቆይቶ በ2015 በጀት ዓመት በሁሉም ዞኖች በማስፋት ውጤታማ ሥራ መሥራት መቻሉን ነው አቶ አለማየሁ የገለጹት፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!