
ደባርቅ: ሐምሌ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዳባት ከተማ አሥተዳደር በ2015 በጀት ዓመት ከክልሉ መንግሥት፣ ከከተማ አሥተዳደሩና ከማኅበረሰቡ በተገኘ 24 ሚሊዮን ብር የተገነቡ የጌጠኛ ድንጋይ ዝርጋታዎችን፣ የጠጠር መንገዶችን፣ የውኋ ማፋሰሻ ቦዮችን፣ የኤሌክትሪክ ዝርጋታዎችንና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን አስመርቋል።
በምርቃቱ የተገኙት የዳባት ከተማ ከንቲባ እንዳልክ ተስፉ በበጀት ዓመቱ ከተማ አሥተዳደሩ ባለው ውስን በጀት፣ በክልሉ መንግሥት ድጋፍና በማኅበረሰቡ ከፍተኛ የገንዘብና የሀሳብ ድጋፍ ችግር ፈች መሠረተ ልማቶችን መገንባት እንደቻለ ተናግረዋል።
ከንቲባው በተጀመረው በጀት ዓመትም አጋሮችን ወደ ከተማዋ በማስገባት የመሠረተ ልማት ሥራዎችን በስፋት ለመሥራት መታቀዱን ተናግረዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች ለመሠረተ ልማት ግንባታው ባሳዩት ትብብር ልክ በየዓመቱ የሚገነቡ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ደኅንነት እንዲጠብቁ አሳስበዋል።
የዳባት ከተማ አሥተዳደር ከተማና መሠረተ ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ያለው ብርሃኔ በ 2015 በጀት ዓመት በ 24 ሚሊዮን ብር አንድ ኪሎ ሜትር የጌጠኛ ድንጋይና የውኃ ማፋሰሻ ቦዮች፣ አንድ ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ፣ አነስተኛ መሸጋገሪያ ድልድዮች፣ የኤሌክትሪክ ዝርጋታና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ገንብተናል ብለዋል። ለመሠረተ ልማት ግንባታው ከወጣው 24 ሚሊዮን ብር ውስጥ 15 ሚሊዮኑ ከማኅበረሰቡ የተሰበሰበ መኾኑን አንስተው ማኅበረሰቡ ለልማቱ ላሳየው ቀና ትብብር ምሥጋና አቅርበዋል።
የዳባት ከተማ ነዋሪ መላእከ ምህረት አዳነ በሬ በመሠረተ ልማት እጦት በተለይ በክረምት የከተማዋ ነዋሪዎች ከአምልኮ ሥርዓትም የሚቀሩበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል። በበጀት ዓመቱ የተገነባው የጌጠኛ ድንጋይ ዝርጋታ ነዋሪዎች አምልኳቸውን በወጉ እንዲፈጽሙ አስችሏቸዋል ነው ያሉት።
ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ እኑዬ ተዘራ ለዓመታት በከተማዋ በነበረው የመሠረተ ልማት እጦት በክረምት ወጥቶ ለመግባት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል። በማኅበረሰቡ የእለት ከእለት ማኅበራዊ ሕይወት ላይም ተጽእኖ ያሳድር ነበር ብለዋል። በ2015 በጀት ዓመት የተከናወኑ የጌጠኛ መንገድ ዝርጋታና ድልድይ ሥራዎች ተጽእኖዎችን በመቀነስ እፎይታን የፈጠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑት የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ተሞክሮዎችን እንዳገኙ የጠቀሱት ነዋሪዎቹ ከተማ አሥተዳደሩ የልማት ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። ቀጣይ ለሚከናወኑ የመሠረተ ልማት ሥራዎችም የቻሉትን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አመላክተዋል።
ዘጋቢ:-አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!