
ባሕር ዳር: ሐምሌ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 6ኛ መደበኛ ጉባኤ ሦስተኛ ቀን ውሎን ቀጥሏል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን የ2015 ዓ.ም የ11 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያዳመጡ የምክር ቤት አባላቱ በቀረበው ሪፖርት ላይ ጥያቄና አስተያየታቸውን አቅርበዋል።
“በፍርድ ቤቶች ላይ የሚስተዋለው ብልሹ አሠራር ፍትሕ እንዲጓደል እያደረገ ነው። ፍትሕን በገንዘብ የሚገዙ አሉ፣ ፍትሕ የጉልበተኞች፣ ፍትሕ በዘመድ ወዳጅ እየተሸጠ ነው” የሚሉ የኀብረተሰብ ምሬቶች እየተሰሙ እንደሆነ በምክር ቤት አባላት ተነስቷል፡፡ የአንዳንድ ዳኞች የሥነ ምግባር ጉድለት፣ ፍትሕ እንዳይረጋገጥ እያደረገ መሆኑም ተነስቷል።
በተለይም አቅመ ደካሞችና ሴቶች ወደ ፍርድ ቤት ሂደው ትክክለኛ ፍትሕ አግኝቶ መመለሳቸው አሳሳቢ ኾኗል ተብሏል።
ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሠጡት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አብዬ ካሳሁን “ሐሰተኛ ምስክርነትና ሐሰተኛ ማስረጃ በከፍተኛ ደረጃ ፍትሕ እንዲጓደል እያደረገ ነው” ብለዋል።
በዳኞች የሚስተዋለው የሥነምግባር፣ የመዝገብ ጥራት ችግር የሚፈጠረውን የፍትሕ መጓደል ለመቀነስ ከብቃት ማሻሻያ እስከ የእርማት እርምጃ እየተወሰደ መኾኑንም ገልጸዋል።
በዋናነት ለፍርድ መጓደል ፈታኝ የኾነው የሐሰተኛ ምስክርና ሐሰተኛ ሰነድ ግን የሁሉንም አካል ትግል የሚጠይቅ ስለመኾኑ በአጽንኦት ተናግረዋል።
በተለይም የሚመጡት ሐሰተኛ ሰነዶች ከተቋማት፣ ሐሰተኛ ምስክሮችም ከኅብረተሰቡ የሚመጡ በመኾናቸው የዳኝነት ሥርዓቱን እየጎዱት ነው ብለዋል። የፍርድ ጥራት እና የፍትሕ አመኔታውን እየበደለው እንደኾነም ነው ያስረዱት።
የዳኞች ሥነምግባር ከትምህርት ሥርዓታችን እስከ ተፈጠረበት ማኀበረሰብ ድረስ ያለውን ክፍተት የሚያሳይ በመኾኑ ብልሹ አሠራርንና ሙስናን መታገል የሁሉም አካል ኀላፊነት እንደኾነ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ አብዬ ካሳሁን በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት በአማራ ክልል በሁሉም እርከን ባሉ ፍርድ ቤቶች በአጠቃላይ ከ750 ሺህ በላይ መዝገቦችን በዓመት ያስተናግዳል ብለዋል።
በዓመት ከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ወደ ፍርድ ቤት ይመጣል ነው ያሉት። የመዝገቦች እና የአገልግሎት ፈላጊው ሕዝብ ብዛት ለጥራትና ቅልጥፍናም ተግዳሮት እንደኾ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!