
ችግሩ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቢስተዋልም ወደ ማዕከሉ እየመጡ ያሉት ታካሚ እናቶች ቁጥር አነስተኛ ነውም ተብሏል፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 14/2012ዓ.ም (አብመድ) ወይዘሮ አለሙሼ ድሪርሳ ወሊድ ላይ ባጋጠማቸው የማኅፀን መውጣት ችግር ምክንያት ሰባት ዓመታትን በአልጋ ቁራኛነት እንዳሳለፉ ነግረውናል፡፡ ከሰውነታቸው የሚወጣው ደም የቀላቀለ ፈሳሽ በማኅበራዊ ግንኙነታቸው ላይ መሠናክል ፈጥሮ እንደነበር ወደኋላ መለስ ብለው አስታውሰዋል፡፡ በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው ፓዊ ሆስፒታል መፍትሔ ለማግኘት ጎራ ብለው የነበረ ቢሆንም በገንዘብ እጦት እልባት ሳያገኙ እንደተመለሱ ገልጸዋል፡፡ የኋላ ኋላ ግን የባሕር ዳር ሃምሊን ፊስቱላ ማዕከል ከቀያቸው መተከል ዞን ጊጶ ወራቦ ጎጥ ድረስ በሠራው የዘመቻ ሥራ መታከማቸውን ተናግረዋል፡፡ ወጪ ሳያወጡም የማኅፀን መውጣት ችግሩ በቀዶ ጥገና ሕክምና ተሠርቶላቸው በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
በቀዶ ጥገና ሥራ ላይ ያገኘናቸው የባሕር ዳር ሃምሊን ፊስቱላ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ቢተው አበበ (ዶክተር) በታኅሣሥ ወር መጀመሪያ አካባቢ ለገበሬ ማኅበራት መልዕክት በማስተላለፍ እናቶች ወደ ማዕከሉ መጥተው እንዲታከሙ ዘመቻ መከፈቱን አስታውቀዋል፡፡ ከአንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካባቢ የማኅፀን መውጣት ችግር አጋጥሟቸው ለመጡ 42 እናቶች የቀዶ ጥገና ሕክምና እንደተረገላቸው ዶክተር ቢተው አንስተዋል፡፡
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም ለ40 እናቶች ቀዶ ጥገናው ተሠርቶላቸዋል፤ ከዚህ በፊትም በተለየ ሁኔታ ለሁለት ሳምንታት ፊስቱላን ጨምሮ የማኅፀን መውጣት ችግር ላለባቸው በቀን ስድስት እናቶች ቀዶ ጥገና ሕክምና እንደተደረገላቸውም ታውቋል፡፡ ነገር ግን በመረጃ እጥረት፣ ባል ስላልፈቀደ በሚል፣ በገንዘብ እጦት እና በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈለገው መልኩ ታካሚ እናቶች ወደ ማዕከሉ እየመጡ እንዳልሆነ ዶክተር ቢተው ገልጸዋል፡፡
ችግሩ በገጠር አካባቢ እንደሚኖር ቢገመትም በማዕከሉ አገልግሎቱን እያገኙ ያሉ እናቶች ጥቂቶች መሆናቸውም ታውቋል፤የማዕከሉ 61 አልጋዎች በቂ ታካሚ ባለመገኘቱ ሙሉ አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑንም ነው የተገለጸው፡፡ በቀጣይ ሁለት ወራትም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እና በብዙኃን መገናኛ በመደገፍ ተመሳሳይ የነፃ ሕክምና ዘመቻ እንደሚኖር አስታውቀዋል፡፡
ባለሙያዎች እንደሚሉት የማኅፀን መውጣት ችግር በከፍተኛ የሥራ ጫና እና በወሊድ ምክንያት ይከሰታል፡፡ የባሕር ዳር ሃምሊን ፊስቱላ ማዕከል የሽንትና ሰገራ መቆጣጠር አለመቻል እና የማኅፀን መውጣት ችግር ላለባቸው እናቶች እንዲያገግሙ ከማድረግ ጀምሮ ቀዶ ጥገና እና ወደ ቤት ሲመለሱም ራሳቸውን እንዲችሉ ዕርዳታ ያደርጋል፡፡
ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ
