
ባሕር ዳር: ሐምሌ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ እያሱ ሳህሌ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የቀበሌ 15 ነዋሪ ናቸው። አቶ እያሱ የመጀመሪያ ልጃቸው የአዕምሮ ውስንነት ችግር አለበት። ችግሩን ተቋቁመው አሳድገውታል።
ሕፃኑ አምስት ዓመት በሞላው ጊዜ ችግሩን እንዳወቁት የሚናገሩት አቶ እያሱ በወቅቱ አስደንግጧቸዋል። ትምህርት አግኝተው ችግሩ መርገም ወይም የእግዚአብሔር ቁጣ እንዳልኾነ እስከሚረዱ ድረስ ብዙ ጭንቀት ነበረባቸው። ባወቁ ጊዜም በችግሩ ውስጥ ያሉ ልጆችን ሊያስተምር የሚችል ትምህርት ቤት ብዙ ባለመኖሩ ፈለገአባይ ትምህርት ቤት አስገቡት። የእሳቸው ልጅ ችግር ብቻ የመሰላቸው አባት ችግሩ የብዙ ሕፃናት መኾኑን ተረዱ።
ልጃቸው የእጅ ሥራ መሥራት ቢወድም አዕምሮው አንድ ቦታ ላይ ተረጋግቶ ባለመሥራቱ ችግር ቢኾንባቸውም ጫና ማሳደር ግን አልፈለጉም። ሙዚቃ ማዳመጥ የሚወደው ልጃቸው እንደሌሎች ልጆች እንዲንቀሳቀስ አብረውት ይወጣሉ። በሚንቀሳቀሱበት ሁሉ ይዘውት ይሔዳሉ። በሥራ ምክንያት ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩም ከእናቱ ጋር ስለሚኾን አብዛኛውን ችግር የሚጋፈጡት እናቱ መኾናቸውን የገለጹት አቶ እያሱ ችግሩ ብዙ ቢኾንም “ልጃችን ለእኛ ጌጣችን ነው ዛሬም እንንከባከበዋለን፣ እንጠብቀዋለን” ይላሉ። ልጃቸው እንዳይጎልበት የሚቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉም ነው ያስገነዘቡት። ወላጆች የልጆችን ፍላጎት በማሟላት መንከባከብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የልዩ ፍላጎት እና አካቶ ትምህርት ፕሮግራም መምህር ረድኤት መስፍን (ዶ.ር) እንደሚሉት የአዕምሮ እድገት ውስንነት ማለት በማኅበረሰቡ ውስጥ አማካይ ከሚባለው የአዕምሮ የብስለት መጠን በታች ሲኾን፣ መሠረታዊ የእለት ከእለት እንቅስቃሴዎችን መተግበር ሲያቅተው፣ ለምሳሌ መግባባት፣መመገብ፣ መልበሥ፣ መጸዳዳት የመሳሰሉትን በእድሜው መጠን መተግበር ካልቻለ እና ይኽ ችግር ከ22 ዓመት በፊት መታየት ከጀመረ ልጆች የአዕምሮ እድገት ውስንነት አለባቸው ይባላል።
የአዕምሮ እድገት ውስንነት ይኸነው የተባለ መንስኤ የለውም ይላሉ። ነገር ግን በማኅበረሰቡ የተሳሳተ አመለካከት የሚነሱ ጽንሰ ሃሳቦች መኖራቸውን ይገልጻሉ። የፈጣሪ ቁጣ ነው፣ የዘር ነው የሚሉ ሃሳቦች ዋናወቹ መኾናቸውንም ነው ያነሱት።
የአዕምሮ እድገት ውስንነት እናት ነፍሰጡር በነበረችበት ወቅት በሚያጋጥማት የስነ ሕይወት እና የአካባቢ እክሎች ጋር ተያይዞ የሚመጣ ችግር፣ በወሊድ ጊዜ በሚፈጠር የተራዘመ ምጥ እና ምጡን ለማስታገሥ በሚወሰዱ እርምጃዎች፣ ከወሊድ በኋላ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ሕፃናት ተገቢውን እንክብካቤ ካለማግኘት፣ ወይም ከባድ ወረርሽኝ ለችግሩ በመንስኤነት ይነሳሉ ብለዋል።
የአዕምሮ እድገት ውስንነት ደረጃዎች አሉት። ትንሽ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው፣ መካከለኛ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው፣ ከፍተኛ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው እና የእድሜ ልክ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ተብለው እንደሚከፈሉም አስረድተዋል። የአዕምሮ እድገት ውስንነት እና የአዕምሮ በሽታ አንድአይነት አይደሉም። በሽታ የሚባለው አንድ ሕፃን በራሱ መብላት መጠጣት መልበስ ጀምሮ ድንገት በተፈጠረ ችግር ይህ ሂደት ቢቋረጥ የሚመጣው ችግር የአዕምሮ ሕመም ይባላል። የአዕምሮ እድገት ውስንነት የእድሜ ደረጃውን ጠብቆ መመገብ መልበሥ ካልቻለ እና ውስንነት ካለ ለዚህ ችግር ተጋልጧል እንላለን ብለዋል።
በኢትዮጵያ ደረጃ የሚያስማማ መስፈርት ባይኖርም ባለባቸው ችግር እና በሚፈልጉት እገዛ መጠን ተመሥርቶ ልየታ እንደሚካሄድ ዶክተር ረድኤት ተናግረዋል። ዶክተር ረድኤት ለልጆች ባላቸው ውስንነት ተመሥርቶ ተገቢ የኾነ ጥራት ያለው ድጋፍ እና እንክብካቤ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!