‹‹ሕጋዊ መሆን አለመሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት የተማሪዎችና ተቋማት ነው፡፡›› የከፍተኛ ትምህርት አግባብነት እና ጥራት ኤጄንሲ

421

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 14/2012ዓ.ም (አብመድ) ከግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀዉ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተቀጠሩ ሠራተኞች ሕጋዊ መሆን አለመሆናቸዉን የማረጋገጥ ኃላፊነቱን የተመረቁበት ተቋም ወይም ተመራቂዎች እንዲወስዱ የማድረግ እርምጃ እንደሚወስድ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነት እና ጥራት ኤጄንሲ አስታወቀ፡፡

ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው እና አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን ሳያሟሉ ተማሪዎችን እያስመረቁ ያሉ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለምሩቃን የሚሰጡት ዕውቀት እና ክህሎት በቂ ባለመሆኑ በሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነም ኤጀንሲው ገልጿል፡፡

በማንኛውም ተቋም የሚሰጡ የከፍተኛ ትምህርት ስልጠናዎች ደረጃቸውን የጠበቁ አግባብነትና ጥራት ያላቸው መሆናችውን ማየት፣ የከፍተኛ ትምህርት ስልጠናዎች ከሀገሪቱ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ሌሎች አግባብነት ያላቸው ፖሊሲዎችን ጋር መገናዘባቸውን ማረጋገጥ፣ በተቋቋመበት አዋጅ መሠረትና አግባብነት ባላቸው ሕጎች መሠረት ለኤጄንሲው የቀረበን የዕውቅና ወይም የዕድሳት ፈቃድ ጥያቄ መርምሮ ለሚኒስትሩ የውሳኔ ሐሳብ ማቅረብ እና ተቋማቱ ያሉበትን ሁኔታና ደረጃ በየጊዜው ለሕዝብ በተለያዩ መንገዶች ማሳወቅ ከከፍተኛ ትምህርት አገባብነትና ጥራት ኤጄንሲ ስልጣንና ተግባራት መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

የከፍተኛ ትምህርት አግባብነት እና ጥራት ኤጄንሲ ዋና ዳይሬከተር አንዱዓለም አድማሴ (ዶክተር) ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚቀላቀሉ ተማሪዎች ተመርቀው ከወጡ በኋላ በሚፈልጉት መስክ ተሠማርተው ሀገራቸውንና ራሳቸውን እንዲጠቅሙ የስልጠናው ጥራት እና አግባብነት አስፈላጊ መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር አንዱዓለም ‹‹ተማሪዎች በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለመማር ሲወስኑ የተቋሙን ሕጋዊ ዕውቅና፣ ፕሮገራም እና ‹ሞዳሊቲ› ግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው›› ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር አንዱዓለም እንዳሉት ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው እና አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን ሳያሟሉ እያስተማሩ እና እያስመረቁ ያሉ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለምሩቃን የሚሰጡት ዕውቀት እና ክህሎት በቂ ባለመሆኑ በሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡

ከግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተቀጠሩ ሠራተኞች ሕጋዊ መሆን አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ ኃላፊነቱን ተቋሙ ወይም ተመራቂዎች እንዲወስዱ የማድረግ እርምጃ እንደሚወሰድ ዋና ዳይሬክተሩ ለአብመድ ገልጸዋል።

ተጠሪነቱ ለትምህርት ሚኒስቴር የሆነዉ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጄንሲ ራሱን የቻለ ሕጋዊ ሰውነት ያለው አካል ሆኖ በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 351/1995 የተቋቋመ የመንግሥት ተቋም ነው፡፡

ዘጋቢ፦ በለጠ ታረቀኝ -ከአዲስ አበባ

Previous articleየባሕር ዳር ሀምሊን ፊስቱላ ማዕከል የማኅፀን መውጣት ችግር ላጋጠማቸው 42 እናቶች የቀዶ ጥገና ሕክምና ሰጠ፡፡
Next articleየኢንዱስትሪ መሠረተ ልማቶችን ከማሟላት በዘለለ በግብዓት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡