
ባሕር ዳር: ሐምሌ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የፋይናንስ ጉዳዮች፤ የኢኮኖሚ ዕቅድና ውህደት ላይ ያተኮረው የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ጉባኤ በናይሮቢ ኬንያ እየተካሄደ ይገኛል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ጥሩማር አባተ በሚኒስትሮች ደረጃ እየተደረገ ባለው ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ሚኒስቴር ዴኤታዋ አፍሪካ ከችግሮች ባሻገር በኢንቨስትመንት፤ ዘላቂ ዕድገትና የጋራ ብልጽግናን ማስፈን በሚል ርዕስ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ ሃሳቦችን አንስተዋል።
የአፍሪካ ሀገራት በህገወጥ መልኩ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪንና ፋይናንስን ከመከላከል አኳያ ጠንካራ ስርዓት መገንባትና ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ማስወገድ እንደሚገባ፣ ዘላቂ ልማትንና ኢንቨስትመንትን ከማሳደግ አኳያ የአፍሪካ መንግስታት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰቱ ችግሮችን መፍታት፤ የግሉ ሴክተርና የመንግስት አጋርነትን በማጠናከር የመሰረተ ልማት አውታሮችን መዘርጋት አስፈላጊነቱን አጽንዖት ሰጥተው አብራርተዋል።
በጉባኤዉ የአፍሪካ አካታች ዕድገትና ዘላቂ ልማትን በሚወስኑ ሁኔታዎች ዙሪያ ላይ መወያየት፤ የአፍሪካ ክልላዊ ውህደት የደረሰበትን ደረጃ በመገምገም በቀጣይ የአፍሪካ ሀገራት ለውህደቱ የራሳቸውን የማይተካ ሚና እንዲጫወቱ በማድረግ ላይ ምክክር እየተደረገበት እንደሚገኝ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
በፓናሉ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ጥሩማር አባተ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዉባቸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!