የአማራ ክልል ሕዝብ መሰረታዊ የኾኑ የማንነት ጥያቄዎች በሕግ የጸኑ እንዲኾኑ ተጠየቀ።

102

ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሕዝብ መሠረታዊ የኾኑ የማንነት ጥያቄዎች በሕግ የጸኑ እንዲኾኑ የክልሉ ምክር ቤት አባላት ጠይቀዋል። የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ራያ እና ጠለምት አካባቢ ሕዝብ ከህወሃት ግፍና ጭቆና ተላቆ መልሶ ያገኘውን ጥንተ አማራዊ ማንነት መንግሥት በሕግ አጽንቶ፣ በጀትም በጅቶ እንዲያለማ ማስቻል እንዳለበት የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት በጉባዔው ላይ አንስተዋል። እነዚህ አካባቢዎች እንደ ኢትዮጵያዊነታቸው ማግኘት የሚገባቸው የማንነትና የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ሕጋዊ ጥያቄዎች መልስ ሊሰጣቸው እንደሚገባ በምክር ቤቱ ተነስቷል።

ለምክር ቤት አባላት ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) የማንነት ጉዳይ ላለፋት አራት አስርት ዓመታት መሰረታዊ የኢ-ፍትሐዊነት መገለጫ ኾኖ ቆይቷል ነው ያሉት። ጉዳዩ ዘላቂ እልባት ማግኘት የሚገባው ነው ሲሉም ተናግረዋል። የአካባቢዎቹ የቆየ የማንነት ጥያቄ በሕግ የጸና እንዲኾን አፋጣኝ መልስ መሥጠት ለነገ የማይባል ጥያቄ ነውም ብለዋል።

“የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ራያ እና ጠለምት አካባቢዎችን በተመለከተ የአማራ ክልል መንግሥት እና ሕዝብ ተቀዳሚ ተግባር ነባራዊ እውነታን ይዞ ማስረዳት ነው” ሲሉም ርእሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተለያዩ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ ።
Next articleየአማራ ክልል ምክር ቤት የሶስተኛ ቀን ጉባዔውን ጀምሯል።