
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 13/2012ዓ.ም (አብመድ) በሞጣ ከተማ አስተዳደር ከሃይማኖት አባቶች፣ ሀገር ሽማግሌዎች እና የኅብረተሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
የክልሉ ሠላምና ደኅንነት ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች፣ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሃይማኖት መሪዎች በተገኙበት ነው ውይይት የተደረገው፡፡
በውይይቱ ታኅሣሥ 10/2012ዓ.ም የተከሰተው ክስተት የሞጣ ከተማ የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን የማይወክል መሆኑ ተነስቷል፡፡ ሞጣ ከአመሠራረቷ ጀምሮ ሁለቱም ሃይማኖት ተከታዮች በፍቅር፣ በመተባበር እና በአንድነት የሚኖሩባት ከተማ እንደሆነች አብነቶች በተሳታፊዎች ተነስተዋል፡፡
‹‹አብያተ ክርስቲያናት ሲታነጹ ሙስሊሙ በገንዘብም በጉልበትም አስተጽኦ አድርጓል፤ መስጂዶች ሲታነጹም ክርስቲያኑ ተመሳሳይ ሚና ነበረው›› ተብሏል፡፡ በሠርግ ወቅት ክርስቲያን ከደገሰ ለሙስሊሙ እርድ እንደሚዘጋጅ እና ሙስሊሙም ከደገሰ ተመሳሳይ ዝግጅት እንደሚደረግ አንስተዋል፡፡
ይህ አንድነታቸው በተፈጠረው ወቅታዊ ችግር እንደማይላላ እና በመነጋገር እንደሚፈቱትም ተወያዮቹ አስታውቀዋል፡፡
በመንግሥት በኩል የችግሩን ጠንሳሾች፣ ተሳታፊዎች እና ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አጣርቶ ተጠያቂ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶች ምዕመኑን በማረጋጋትና ወጣቱን በመምከር ሞጣ የቀድሞ ሠላሟ እንዲመለስ አሳስበዋል፡፡ ቤተ እምነቶችን በጋራ መልሰው እንደሚገነቡ፣ ከፀጥታ አካላት ጋር በየደረጃው ኮሚቴ በማዋቀር ችግሩን የማጣራት፣ ንብረት የማስመለስ እና ተጎጂዎችን የማቋቋም ሥራ ለመሥራትም ተግባብተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ አብርሃም ‹‹የተቃጠሉት ቤተ እምነቶች ባለቤትነታቸው የሁለቱም ሃይማኖት ተከታዮች ናቸው፤ መስጂድ ስለተቃጠለ የሚደሰት ክርስቲያን፣ ቤተ ክርስቲያን ስለተቃጠለ የሚደሰት ሙስሊም የለም፤ ሊኖርም አይገባም፡፡ አሁንም ቤተ እምነቶችን በጋራ መገንባት ይገባል፤ ወጣቶችን ከስሜታዊነት እንዲቆጠቡ እናድርግ›› ብለዋል፡፡
የዑለማ ምክር ቤት አባል ሼህ መሐመድ ሲራጅ ደግሞ በችግሩ ማዘናቸውን እና ‹‹ኅብረተሰቡን በሃይማኖት በመከፋፋል አገር ለማፍረስ ሌት ተቀን የሚተጉ አካላት›› ያሏቸው ተመሳሳይ ሥራዎች በሀገሪቱ እየሠሩ መሆኑን በማመልከት ነዋሪው ሊነቃ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ኅብረተሰቡ በአንድነት በመቆም ሴራዉን ማፍረስ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡ ችግር በተከሰተ ጊዜም ሕዝቡ በአንድነት በመቆም በጥላቻ አለመተያዬቱን ማስታወቅና ኢትዮጵያዊ ዕሴቱን ማስቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸህ ሰይድ አህመድ እስልምና በኢትዮጵያ የተስፋፋበትን ታሪክ በማውሳት ይህን መቻቻል እና አብሮ የመኖር ዕሴት ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ኅብረተሰቡ እርስ በእርስ በጥርጣሬ መተያዬት እንደሌለበትና በአንድነት በመቆም ጠላቶቹን ሊያሳፍር እንደሚገባም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
የአማራ ክልል ሠላምና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አገኘሁ ተሻገር በውይይቱ ማጠቃለያ ከማረጋጋቱ ባለፈ የምርመራ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹የችግሩ ተሳታፊ የሆኑና ችግሩን በመከላከል ረገድ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ አካላት ጭምር ተጠያቂ ይሆናሉ›› ብለዋል አቶ አገኘሁ፡፡ ውይይቱ በየደረጃው እንደሚቀጥል እና ለሠላም፣ ለመነጋገር ቅድሚያ ተሰጥቶ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡ በመጨረሻም አጣሪ ኮሚቴ ተዋቅሮ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡
ዘጋቢ፡- የማነብርሃን ጌታቸው
