
ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተለያዩ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል። በዘላቂ ልማት ላይ ያተኮረው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የፖለቲካ መድረክ በኒው ዮርክ ከተማ እየተካሄደ ነው። አምባሳደር ምስጋኑ ከመድረኩ ጎን ለጎን ከተመድ የሰላም ማስከበር ረዳት ዋና ፀሐፊ ጂን-ፒየር ላክሮክስ ጋር በሰብአዊ ጉዳዮች እና በሰላም ማስከበር ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
አምባሳደሩ በተጨማሪም ከተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሐፊ እና ከድርጅቱ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (ኦቻ) ምክትል የአደጋ ጊዜ አስተባባሪ ጆይስ ምሱያ ጋር ተወያይተዋል። ሚኒስትር ዴኤታው በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር “ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተያዙ የዘላቂ የልማት ግቦችን እያሳካች ነው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ በተመድ የተያዙ ዘላቂ የልማት ግቦች እንዲሳኩ ከአገራዊ በጀቷ ከፍተኛውን ድርሻ ለዘላቂ ልማት ግቦችና ለድህነት ቅነሳ ፖሊሲዎችና መርሐ-ግብሮች በተለይም እንደ አየር ንብረት ላሉ ዘርፎች በመመደብ ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ልዩ ትኩረት በመስጠት ቁርጠኛ መሆኗን አመልክተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!