
ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በተጠናቀቀው 2015 በጀት ዓመት ለዓባይ ግድብ ግንባታ ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት ባለፈው 2015 በጀት ዓመት ለዓባይ ግድብ አንድ ቢሊየን 447 ሚሊየን 352 ሺህ 343 ብር ተሰብስቧል፡፡
ከሀገር ውስጥ ቦንድ ሽያጭ አንድ ቢሊየን 147 ሚሊየን 784 ሺህ 738 ብር ተሰብስቧል ያሉት ወይዘሮ ፍቅርተ፤ ከዲያስፖራው 40 ሚሊየን 106 ሺህ 603 ብር ተሰብስቧል፡፡ በአጭር የጽሁፍ መልዕክት 146 ሚሊየን 241 ሺህ 251 ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል። በስጦታ የተሰበሰበ 113 ሚሊየን 219 ሺህ 750 ብር ገቢ መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡ እንደ ኢፕድ ዘገባ በአጠቃላይ ግድቡ ከተጀመረ አንስቶ እስከ ሰኔ 30/2015 ዓ.ም 18 ቢሊየን 350 ሚሊየን 866 ሺህ ብር በላይ ተሰብስቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!