
ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የበጀት ዓመቱን የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለምክር ቤት አቅርቧል። ሪፖርቱን ያቀረቡት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አብዬ ካሳሁን በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ በሁሉም እርከን ፍርድ ቤቶች 674ሺህ 785 መዝገቦች እልባት ማግኘታቸውን ተናግረዋል። የፍርድ ቤት የዳኝነት አገልግሎትን ለማሻሻል ልዩ ልዩ አሠራሮች ተግባራዊ መደረጋቸውን በሪፖርታቸው አንስተዋል።
እርቅ ተኮር የፍትሕ አሥተዳደር፣ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እና ልዩ ልዩ ሕጎችን አውጥቶ መተግበር ላይ አበረታች ሥራዎች መሠራታቸውን ነው የተናገሩት። ፕሬዚዳንቱ በሪፖርታቸው እንደጠቀሱት በበጀት ዓመቱ 11 ወራት አፈጻጸም እልባት ካገኙ 546ሺህ 342 የፍትሐብሔር ጉዳዮች መካከል 29ሺህ 213 ጉዳዮች በእርቅ እልባት ያገኙ ናቸው ብለዋል።
በክልሉ ፍርድ ቤቶች ከሚቀርቡ ጉዳዮችም መሬትን የሚመለከቱ ጉዳዮች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ ነው የገለጹት።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!