የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በግጭቱ የተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሰብል ሰበሰቡ፡፡

128

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 13/2012ዓ.ም (አብመድ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በታኅሣሥ መጀመሪያ ሳምንት በተፈጠረ ችግር የተጎዱ የመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሰብል ሰብስበዋል፡፡ በዞኑ ዳንጉር ወረዳ ማምቡክ ከተማ በጎ አድራጎት ማኅበር መሥራችና ሊቀ መንበር የሱፍ እጅጉ እንደተናገረው ሰሞኑን በወረዳው በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ሰብል የመሰብሰብ ዘመቻ ተካሂዷል፡፡

በሰብል ስብሰባው ላይ የተሠማሩት ደግሞ የቤኔሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የፀጥታ አካላት፣ ወጣቶች እና የማምቡክ ከተማ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ በቀጣይም ከከተማውን ቴክኒክና ሙያ እንዲሁም የተለያዩ ‹ሴክተር› መሥሪያ ቤቶች ጋር በመነጋገርና ከአምስት አጎራባች ወረዳዎች ጋር በመቀናጀት የስጋት ቀጠና ተብለው በሚታሰቡ አካባቢዎች ሰብል የመሰብሰብ ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የሱፍ የተናገረው፡፡

በክልሉ አሁን የብልጽግና ፓርቲ አካል የሆነው አዴፓ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተመሥገን ኃይሉ ወጣቶችን እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር ትናንት ታኅሣሥ 12/2012 ዓ.ም እና ዛሬ የሦስት ተጎጂዎችን ሰብል ሙሉ በሙሉ መሰብሰቡን አስታውቀዋል፡፡ ችግሩ ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ የፀጥታ ኃይሉ በየቦታው ተሠማርቶ አርሶ አደሮች ያለምንም ስጋት ሰብላቸውን እንዲሰበስቡ እያደረገ እንደሚገኝ ነው አቶ ተመሥስገን የተናገሩት፡፡ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም ለአንድ ሳምንት ያህል በአካባቢው ተሰማርተው ሕዝቡን የማረጋጋትና ወንጀለኞችን ለሕግ የማቅረብ ተግባር እያከናወኑ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ተመሥገን ማብራሪያ ችግሩ ለአንድ ቀን ከተፈጠረ በኋላ ምንም ዓይነት የፀጥታ መደፍረስ አልተፈጠረም፡፡ በቀጣይም ችግሩ እንዳይፈጠርና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ በዘላቂነት እንዲጠናከር ከመጪው ሐሙስ ጀምሮ የእርቀ ሠላም ኮንፈረንስ ለማድረግ ዕቅድ ተይዟል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous articleበፀጥታ ችግር ከትምህርት ገበታ ለተፈናቀሉ ተማሪዎች ምላሽ እንዲሰጥ የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጠየቁ፡፡
Next article‹‹የችግሩ ተሳታፊ የሆኑና ችግሩን በመከላከል ረገድ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ አካላት ጭምር ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡›› አቶ አገኘሁ ተሻገር