“በአንድነት እንጂ በመከፋፈል የሚረጋገጥ ሰላም፤ የሚመጣ ልማትም የለም” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

77

ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት የክልሉን ወቅታዊ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ አስመልክቶ ላነሱት ጥያቄና አስተያየት ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተውበታል።

ርእሰ መሥተዳድሩ እንደተናገሩት መንግሥት መንግሥታዊ ኀላፊነቱን ለመወጣት ይሠራል ብለዋል። በክልሉ የታጠቁ ኀይሎች በሕጋዊ መንገድ ለሰላምና ውይይት ቀናኢ እንዲኾኑ ርእሰ መሥተዳደሩ ጠይቀዋል። በሕጋዊ መንገድ መደራጀት፣ ጥያቄያቸውንም ማቅረብ እንደሚገባቸው ነው የጠቆሙት።

ከክልሉ ልዩ ኀይል መልሶ መደራጀት ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ችግር በተሳሳተ መንገድ ትርጉም ተሰጥቶት ዋጋ እንዳስከፈለም አንስተዋል። መንግሥት ልዩ ኀይሉ የበለጠ ይደራጅ፣ ይታጠቅ እንጂ ይበተን የሚል ዓላማ የለውም ሲሉ አስገንዝበዋል። ሪፎርሙ ልዩ ኀይሉን የሚበትን ኀይል፣ መሳሪያውንም እንዲያወርድ የሚያደርግ ሳይኾን ለበለጠ ሀገራዊ ተልእኮ በፍላጎቱ እንዲመደብ ነበር የተሠራው ነው ያሉት።

በክልሉ ውስጥ አንድነትን ለማምጣት ሰላማዊ ውይይትና ምክክር አስፈላጊ ነው ብለዋል። በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታና የሰላም ችግር በሰከነ መንገድ እንዲፈታ ተባባሪ መኾን ይገባልም ነው ያሉት። “ሕዝቡ መንግሥትን ሕግ እንዲያስከብርለት መደገፍ፣ እምነትም መጣል አለበት” ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።
በምክር ቤት አባላት የተነሳው በምክክር ችግሩን መፍታት ይገባል የሚለው አስተያየት ትክክል ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የሰላም መንገድ እድሎችን ሁሉ መጠቀም ተገቢ ነው ብለዋል። ችግሮቻችን በአንድነት እንጂ በመከፋፈል የሚረጋገጥ ሰላም፣ የሚመጣ ልማትም የለም ብለዋል።

የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ፣ የታቀዱ እድሎችም እንዳይባክኑ ቅድሚያ የሕዝቡን ሰላም፣ የሕዝቡን ደኅንነት ማረጋገጥ ይገባልም ሲሉ አሳሰበዋል። ለዚህም ሁሉም አካል ለሰላም ለውይይት ቅድሚያ መስጠት ይገባዋል ነው ያሉት። ለክልሉ ወደ ዘላቂ ሰላም መምጣት በየደረጃው ያሉ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ ምሁራንና ተጽኖ ፈጣሪ ወጣቶችን መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር ይልቃል ጅምሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleወልቃይትን መልሶ ለማልማት የአካባቢው ተወላጆች፣ የልማት አጋሮች እና ሕዝቡ እንዲረባረቡ ጥሪ ቀረበ፡፡
Next article“በበጀት ዓመቱ ከ674 ሺህ በላይ መዝገቦች እልባት አግኝተዋል” ጠቅላይ ፍርድ ቤት