ወልቃይትን መልሶ ለማልማት የአካባቢው ተወላጆች፣ የልማት አጋሮች እና ሕዝቡ እንዲረባረቡ ጥሪ ቀረበ፡፡

58

ሁመራ: ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሕዝብ የነጻነት ምልክት ናት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የምትገኘው ወልቃይት ወረዳ፡፡ ወልቃይት ከወጣት እስከ አዛውንት፤ ከአርሶ አደር እስከ ሚኒስትር፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ባሉ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ በአሁናዊው የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ምህዳር ውስጥ መዘውር ተደርጋ ትወሰዳለች፡፡

ላለፉት ሦሥት አስርት ዓመታት ገደማ በህወሐት የሃሰት ትርክት እና የሴራ ፖለቲካ ምክንያት ተፈጥሯዊ ማንነታቸውን ተነጥቀው ከነበሩት አካባቢዎች መካከል አንዷ የነበረችው ወልቃይት ከእልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ወደ ቀደመ ማንነቷ ከተመለሰች ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ለነጻነቱ ቀናዒ እና ብርቱ የነበረው የአካባቢው ነባር ሕዝብም ከነጻነት ማግስት ወደ ተደራጀ የልማት ሥራዎች ሲገባ ጊዜ አልፈጀበትም ተብሏል፡፡

ነጻነት የወልቃይት ሕዝብ መሠረታዊ እና የቅድሚያ ቅድሚያ የተሰጠው የትኩረት ማዕከል ነበር ያሉት የወልቃይት ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አቶ ክብረአብ ስማቸው ከነጻነት ማግስት ጀምሮ ሕዝቡ ወደ ተደራጀ የልማት ሥራ ገብቷል ብለዋል፡፡ የአንድ ሕዝብ እና አካባቢ ዘላቂ ነጻነት የሚረጋገጠው ወቅቱ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ሁሉ ሳያቆራርጡ በመተግበር ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ሕዝቡ ከነጻነቱ ማግስት ጀምሮ ለዓመታት ያጣውን የመሰረተ ልማት ፍላጎት እንድናሟላለት ይፈልግ ነበር ብለዋል፡፡

የአካባቢው ሕዝብ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት ጠባቂ ብቻ ሳይኾን ግንባር ቀደም ተሳታፊ ነበር ያሉት አቶ ክብረአብ የወረዳዋን ዋና ከተማ ወፍ አርግፍ የመሠረተ ልማት ክፍተት ለማሟላት ከሀገር ውስጥ እስከ ሀገር ውጭ ያሉ የወረዳዋ ተወላጆች ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል ብለዋል፡፡ ከተማዋ እጅግ ቀደምት የምትባል የመልማት አቅም እና ፍላጎት የነበራት ከተማ ብትኾንም በህወሐት ዘመን እሱን አልታደለችም ነበር፡፡ ወፍ አርግፍ ክረምት በጭቃ፣ በጋ ላይ ደግሞ በአቧራ የምትሰቃይ ከተማ ነበረች የሚሉት አቶ ክብረአብ ነዋሪዎቿ በተደጋጋሚ ያነሱት የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ምላሽ አጥቶ ቆይቷል ብለዋል፡፡

አካባቢው ከግፍ አገዛዝ ነጻ ከኾነበት ማግስት ጀምሮ ጊዜያዊ አሥተዳደሩ የሕዝቡን የመልማት ፍላጎት መሠረት ያደረገ ምላሽ ለመስጠት እልህ እና ቁርጠኝነት ብቻ ይዞ የተነሳ ነበር ብለዋል፡፡ በመካከሉ ለዳግም ወረራ እና ጦርነት የተደረጉ ሙከራዎች በተወሰነ ደረጃ የልማት ሥራውን ቢያዘገዩትም ፈጽሞ እንዲቆሞ ግን አላደረጉትም ነበር ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በውስን የሰው ኃይል፣ አካባቢው በነበረው ጸጋ እና በሕዝቡ ድጋፍ የከተማዋ ዋና ዋና አካባቢዎች የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ሥራ ተሰርቷል ነው ያሉት፡፡

በሁለት ዙር ዘመቻ ከአካባቢው ተወላጆች በተሰበሰበ እና ከውስጥ ገቢ በተገኘ 6 ሚሊዮን ብር ገደማ የጥርጊያ መንገድ ዝርጋታ፣ የአነስተኛ ድልድይ ግንባታ እና የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል አቶ ክብረአብ፡፡ በወረዳው ውስጥ አሁን በዋርካ ጥላ ስር የሚማሩ ተማሪዎች አሉ ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ወረዳው ያለውን የሕዝብ ቁጥር የሚመጥን የህክምና መስጫ ጤና ጣቢያ እንደሚጎድለውም አንስተዋል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ከሕዝብ በሚሰበሰብ ድጋፍ እና ከወረዳው የውስጥ ገቢ አስተባብሮ አንድ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት እና ጤና ጣቢያ ለመገንባት አቅደናል ብለዋል፡፡ ከነጻነት ማግስት ጀምሮ የተገነቡ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ምረቃ እና ጉብኝት በቅርቡ ይካሄዳል ያሉት አቶ ክብረአብ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን የሚመለከቱ እንግዶች ለሌላ ዙር የልማት ዘመቻ አጋር የሚኾኑበትን አጋጣሚ ለመፍጠር ወረዳው መዘጋጀቱንም አንስተዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በወልቃይቴዎች ላይ ከተፈጸመው ሰብዓዊ ጉዳት ባለፈ የመሰረተ ልማት ግንባታ አድሎም ነበር ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው የሕዝቡን ሥነ-ልቦና ለመጠገን እና የተፈጠረውን የልማት ክፍተት ለመሙላት ቀን ከሌሊት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች፣ የልማት አጋሮች እና ሕዝቡ ወልቃይትን መልሶ ለማልማት እንዲረባረብም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ:- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በፈታኝ ችግር ውስጥም ኾነን በክልሉ የተፈጠረው የሥራ እድል አበረታች ነው” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)
Next article“በአንድነት እንጂ በመከፋፈል የሚረጋገጥ ሰላም፤ የሚመጣ ልማትም የለም” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)