
ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የምክር ቤት አባላት የሥራ እድል ፈጠራ እና የሥራ አጥነት ችግር ላይ ላነሱት ጥያቄና አስተያየት ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በክልሉ በጊዜያዊነትና በቋሚነት የተፈጠረው የሥራ እድል የሚያበረታታ ነው ብለዋል በሰጡት ማብራሪያ። በተለይም በፋብሪካዎች የተፈጠረው የሥራ እድል ለወደፊቱም ተስፋ የሚጣልበት ስለመኾኑ ነው የተናገሩት።
በበጀት ዓመቱ በክልሉ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሥራ ፈላጊ ዜጎች ተመዝግበው ለ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏልም ነው ያሉት። ከ46 በመቶ በላይ የሥራ እድል የተፈጠረው በኢንዱስትሪዎች መኾኑንም አንስተዋል። 21 በመቶው ደግሞ በአገልግሎት ዘርፍ መኾኑንም ነው የጠቀሱት።
ለሥራ እድል ፈጠራው ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ተሠርቷል ያሉት ዶክተር ይልቃል 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ለሥራ እድል ፈጠራ ብድር እንደዋለም ተናግረዋል።
“በፈታኝ ችግር ውስጥም ኾነን በክልሉ የተፈጠረው የሥራ እድል አበረታች ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ የሥራ እድል ፈጠራው በልዩ ትኩረት ጠንከር ብሎ መሥራትን እንደሚጠይቅም ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ፦ ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!