
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 13/2012ዓ.ም (አብመድ) በዩኒቨርሲቲዎች የተፈጠረውን ችግር በአጭር ጊዜ በመፍታት ወደ ሠላማዊ መማር ማስተማር ሂደት ለመግባት እየተሠራ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር አስታወቀ። በዩኒቨርሲቲዎች ላይ የተፈጠረውን አለመረጋጋት በተመለከተ ከሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች እና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዋናውና ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ግቢ የተማሪ ተወካዮች ጋር ዛሬ ውይይት ተደርጓል።
በምክክሩ የተገኙ ተማሪዎች እንዳሉት ችግሩ የሚፈጠረው በዩኒቨርሲቲዎች የአገልግሎት አሰጣጥ ሳይሆን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና ሀገሪቱን እያስተዳደራት ያለው መንግሥት ክፍተት ነው። ‹‹ለግጭቱ መነሻ አንድን ብሔር በታሪክ ጨቋኝና የበላይ አድርጎ በመሳል በታሪክ መልክ አቅርቦ ማስተማር ነው›› ብለዋል ተማሪዎቹ። በተለይም ለአዳዲስ ተማሪዎች የሚሰጠው የኢትዮጵያ ታሪክ ትምህርት ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያራርቅ በመሆኑ ማስተካከያ እንዲሰጥበት አሳስበዋል። ‹‹የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም እንደሀገር ችግር የሚያመጣ የሀሰት ታሪክ እንደ ትምህርት ሆኖ ሲቀርብ ዝም መባል የለበትም አጽድቆ ማሳለፍም አልነበረበትም›› ነው ያሉት። ‹‹መንግሥት የተማሪዎችን ደኅንነት መጠበቅ ተስኖታል›› ያሉት ተማሪዎቹ ደኅንነታቸው እስካልተጠበቀ ድረስ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በሠላም መማር እንደማይቻልም ነው የተናገሩት። የሚመለከተው አካልም ችግሩ ከመነሳቱ አስቀድሞ የጥንቃቄ ሥራ አለመሥራቱን ተናግረዋል።
ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተፈናቀሉ ተማሪዎች መፍትሔ እስካልተሰጣቸው ድረስ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ሠላማዊ የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ ሊመጣ እንደማይችልም ነው የገለፁት። ‹‹ከሌሎች ዪኒቨርሲቲዎች አንፃር ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሠላም ነው›› ያሉት ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው ስጋት እንጂ አስፈሪ የሆነ ተጨባጭ ችግር እንደሌለም ተናግረዋል።
‹‹የተፈናቀሉት ተማሪዎች በአስቸኳይ መፍትሔ ይሰጣቸው›› ያሉት ተማሪዎቹ ውይይቱ ከሁሉም ተማሪዎች ጋር መሆን እንደሚገባውም ገልፀዋል። ተማሪዎችን በረሀብ መቅጣት ተገቢ አለመሆኑንም አንስተዋል።
‹‹በሠላም ተሠርቶ የሚኖርባት ኢትዮጵያ እየተፈጠረች አይደለም›› ያሉት ተማሪዎቹ ሀገሪቱ ሠላም መሆን ካልቻለች መማርና አለመማር ልዩነት ስለማይኖረው ለሠላም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል። አብዛኛው ተማሪ ከችግረኛ ቤተሰብ የወጣና መማር የማያሻማ ዓላማው እንደሆነም ተናግረዋል።
የፖለቲካ ፓርቲ መብዛት ለትምህርታቸው እንቅፋት እንደሆነም ተማሪዎቹ አንስተዋል። ሰው የሞተባቸው፣ አካል የጎደለባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ክፍተኛ የሆነ ምክክርና ችግር በሚፈጥሩ አካላት እና ተቋማት ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ መቻል እንደሚገባውም ጠይቀዋል። ‹‹ተማሪን ከተማሪ የሚያጋጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚያራምዱ አካላትን እንዴት ነው የምትቆጣጠሯቸው? እውነታውንስ እንዴት ነው የምታወጡት?›› ሲሉም ጠይቀዋል።
ተማሪዎቹ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያለው ችግር ይታወቃል፤ መፍትሔውን ግን የሚፈልግ አካል ጠፍቷል። አንዱ ተማሪ ሌላኛው ደግሞ ተባራሪ ከሆነ አሁንም መማር ማስተማሩን ለማስቀጠል ከባድ ይሆናል። ‹‹አብዛኛው ተማሪ ለመማር ነው የመጣው ነገር ግን ፍትሐዊ የመማር ማስተማር ሥርዓት የለም›› ያሉት ተማሪዎቹ የሕግ የበላይነት እንደግለሰብም እንደተቋምም መከበር እንዳለበት ጠይቀዋል። መንግሥት አጥፊውን የመለዬት አቅም እንደሰጠውና ተማሪዎቹ ተሰሚነት እንደሌላቸውም ገልፀዋል።
መንግሥት የሚተገብረው ፖሊሲ እና የትምህርት መዋቅሩ የሀገሪቱን ባህል፣ ወግና እሴት ያገናዘበ አለመሆኑንም ተናግረዋል። ትውልዱ ሃይማኖቱንና ባህሉን እንዲረሳ ተደርጓል፤ መንግሥትም ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም፡፡ ‹‹የዩኒቨርሲቲዎች ችግር ውስጣዊ ሳይሆን ውጫዊ ነው። መንግሥት ለማይታወቅ ኃይል እጁን ሰጥቷል፤ ተማሪዎች የፖለቲካ ሰለባ ሆነዋል›› ብለዋል። መሠረታዊው ችግሩ የታሪክ መዛባት በመሆኑ ታሪኩ ማስተካከያ መደረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።
‹‹በሀገሪቱ መፍትሔ የሚመጣው የተንኮል ምንጩ ሲደርቅ ነው›› ያሉት ተማሪዎቹ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የሚወሰደው እርምጃ እኩል መሆን መቻል እንዳለበት አሳስበዋል። በዩኒቨርሲቲዎች ለተፈጠረው ችግርና ሞት መንስኤው መንግሥት፣ ተማሪው፣ ዩኒቨርሲቲው ወይስ ሌላ አካል የሚለውን መለዬት እንደሚገባም ጠይቀዋል። ‹‹በአንደኛው ዩኒቨርሲቲ ኮማንድ ፖስት በሌላው ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ሠላማዊ የመማር ማስተማር ዘላቂ መፍትሔ ስለማይሆን ሁሉንም ዩኒቨርሲቲዎች ሠላማቸውን ማስጠበቅ ይገባል›› ነው ያሉት። ተማሪዎችና ወላጆች የፈረሙት ፊርማ ለታሰበው ዓላማ እንዳልዋለና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንዳልተጠቀመብትም ገልፀዋል። መንግሥት ከሰው ሀብት ይልቅ ለቁሳዊ ንብረት እየተጠነቀቀ መሆኑንም ተማሪዎቹ አመልክተዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ዪኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፍሬው ተገኘ (ዶክተር) ‹‹ዴሞክራሲ ‹በሰው ላይ ክፉ አታድርግ፤ የበደለህን አትበድል› ከሚለው የሃይማኖት አስተምህሮ በታች ነው፡፡ ዴሞክራሲ ባዕዳችን አይደለም፤ ሁሉም ለእንዲህ ዓይነቱ መልካም ተግባር ተግዥ መሆን አለበት›› ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው በውይይት ያምናል ያሉት ፕሬዝዳንቱ በዩኒቨርሲቲው አቅም ሊፈቱ የሚችሉ ጉዳዮችን እንዳወያዩም ነው የገለፁት። ውጫዊ ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ ችግር እንዳለበትም ገልፀዋል።
‹‹ስለተፈናቀሉ ተማሪዎች እኛም ያገባናል›› ያሉት ዶክተር ፍሬው ስለ ተማሪዎች ጥያቄ መጠየቅ የሚገባው እየተማሩ መሆን እንዳለበትም ነው የመከሩት። የሕግ የባለይነት በግለሰብም፣ እንደ ዩኒቨርሲቲም እንደ ሀገርም መከበር አለበትም ብለዋል። ተማሪዎችም የችግር ተባባሪ መሆን እንደሌለባቸው ነው የገለፁት። ‹‹መጎዳት ይቅርና ማንንም በስጋት እንዲኖር አንፈልግም›› ያሉት ዶክተር ፍሬው ተማሪዎች በሠላም እንዲኖሩ ያደረገ እንዳለ ሁሉ ተማሪዎች በሠላም እንዳይማሩ የሚያደርጉም መኖራቸውን አስታውቀዋል። ዩኒቨርሲቲው ውጤታማ የሚሆነው ተማሪዎች ጋር መግባባት ሲቻል መሆኑንም ገልጸዋል። የኒቨርሲቲው ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዳይሬክተር ጄኔራል ጌታቸው ተፈራ በበኩላቸው ‹‹የችግሮቹ መነሻ የኢትዮጵያዊነትን ትስስር ለመበጠስ የሚደረግ ጥረት ነው›› ብለዋል። ችግሩ ያለው እኛ ካልመራናት በስተቀር በሚሉ አካላት የሚፈጠር እንደሆነም ገልፀዋል።
ችግር የሚፈጥረው አካል በዕቅድና በበጀት እንደሚንቀሳቀስ ገልፀው በጋራ መታገል እንደሚገባም አሳስበዋል። ‹‹በየዩኒቨርሲቲዎች እንደጸደቀ ተደርጎ ትምህርት ይሰጥበታል የተባለው የኢትዮጵያ ታሪክ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚመለከታቸው አካላት ሐሳብ እንዲሰጡበት እንጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አላጸደቀውም›› ብለዋል። ‹‹ታሪክ ሕዝብ ከሕዝብ ለማገናኜት ይሠራል›› ያሉት ዳይሬክተር ጄኔራሉ ‹‹ሞጂሉ ሐሳብ እንዲሰጥበት እንጂ የጸደቀ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል›› ነው ያሉት።
በዕቅድና በገንዘብ ተደግፎ የሚሠራው አካል ላይ እርምጃ መወሰድና እርምጃውም የሚያረካ መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲዎች ላይ ጠብ የጫሩ ተማሪዎች ጉዳያቸው በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ ተይዞ እየተጣራ እንደሆነም ገልፀዋል። ‹‹መንግሥት ለዩኒቨርሲቲዎች ሠላም ኃላፊነት መውሰድ አለበት፡፡ የተፈናቀሉትን ተማሪዎች መፍትሔ መስጠት መቻል አለበት›› ያሉት ዳይሬክተር ጄኔራሉ በየዩኒቨርሲቲዎች ውይይት እየተደረገ እንደሆነና ውጫዊውም ውስጣዊውም የሠላም ሁኔታ አስተማማኝ መሆኑ ሲረጋገጥ ተማሪዎችን ለመጥራት ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም ገልጸዋል።
‹‹በየክልሎች ይማሩ›› የሚለውን ሐሳብ ለመተግበር ከባድ እንደሆነና ቢተገበር እንኳን የጠላትን ዓላማ ማሳካት ስለሚሆን ይህን ማድረግ መፍትሔ እንደማይሆንም ነው ያመለከቱት። ዩኒቨርሲቲዎችን ሠላማዊ በማድረግ ተማሪዎችን የመመለስ ኦፕሬሽን እየተሠራ እንደሆነም ነው ያስረዱት። ይህን ለማድረግም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ብቻ ሳይሆን የፌዴራል መንግሥትም እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲዎችም መጠበቅ እንዳለባቸው ነው የገለፁት።
ችግር የሚፈጥሩ ተማሪዎችን፣ መምህራንና የአስተዳድር ሠራተኞች ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም ተናግረዋል። የሚሠራው ሥራ አጥፊውን በመለዬት፣ የዩኒቨርሲቲውን ሠላም በማረጋገጥ፣ በመጠበቅ ተማሪዎች ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ እንደሆነም ገልፀዋል። በአንድ ሳምንት ውስጥ ተገምግሞ እንደሚያልቅና ልጆቹን ወደ ነበሩበት የመመለስ ሥራ እንደሚሠራ ነው የገለፁት። በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥም የተለያዩ የፖለቲካ ሐሳቦችን በሚያራምዱ አካላት ላይ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አመላተዋል። ለችግሩ መፍትሔ እንደሚሰጠውም አረጋግጠዋል። ውይይቱ በተለያዩ ግቢዎችም እንደሚደረግ ታውቋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
