
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 13/2012ዓ.ም (አብመድ) በዩኒቨርስቲዎች የሚስተዋለውን የፀጥታ ችግር መንስኤ ለመለየትና ዘላቂ ሠላም ለማምጣት ያለመ ውይይት በደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ እየተካሄደ ነው።
ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና ከክልል የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች በዩኒቨርስቲው የተማሪ ተወካዮችን እያወያዩ ነው።
በውይይቱ የትምህርት ሂደቱን የሚያደናቅፉ አዝማሚያዎችን ቀድሞ መከላከልና ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ተገቢ መሆኑ ተመላክቷል። ችግር እየፈጠሩ ያሉ አካላት ላይ መንግሥት እርምጃ መወሰድ እንደሚገባና የተማሪዎች ደኅንነት ሊጠበቅ እንደሚገባ በተማሪዎች ሐሳቦች ተነስተዋል።
‹‹በዩኒርሲቲዎች የሥነ ምግባር ትምህርት ሊሰጥ ይገባል። ችግሩ እንዲባባስ ጥላቻን የሚያራግቡ ሚዲያዎች ላይም እርምጃ ይወሰድ፡፡ ተማሪዎች የፖለቲካ መጠቀሚያ ከመሆን ወጥተን ለሀገር አንድነት መቆም አለብን›› የሚሉ ሐሳቦችንም ተማሪዎቹ አንስተዋል፡፡
ችግር ፈቺ እንጂ ችግር ፈጣሪ መሆን እንዴለባቸው ያነሱት ተወያይ ተማሪዎቹ በፀጥታ ችግርና በስጋት ከዩኒበርስቲ የወጡና ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎች አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል።
ተመሳሳይ ውይይቶች በአማራና ኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ከ20 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚካሄዱም ታውቋል፡፡
ዘጋቢ፡- አማረ ሊቁ -ከደብረ ታቦር
