ትናንት ናፈቀኝ!

437

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 13/2012ዓ.ም (አብመድ) 1974ዓ.ም ሚያዝያ 26 ቀን ዕለተ ረቡዕ ሊነጋ ሲል ይህችን ምድር ተቀላቀልኩ። የልጅነት ጊዜየን ብዙም አልወደውም። ‹ለምን?› እንዳትሉኝ፤ ነገር ግን ዛሬ እየሆነ ያለውን ሳዬው ልጅነቴ ናፈቀኝ።

ያደኩት ስማዳ ወረዳ ወገዳ ከተማ ቀጠና 3 ነው። ከቤታችን በቅርብ ርቀት መስጅድ አለ። ብዙ ሙስሊሞችም ይኖራሉ። የሚገርመው ነገር ግን የእኔ ጓደኞች የሚበዙት ክርስቲያን ናቸው። ስለሃይማኖት አውርተን አናውቅም። ከስጋ በስተቀር ሁሉንም አብረን እንበላለን።

ከምግብ ጋር በተያያዘ ሁለት ገጠመኞች አሉኝ፤ መቸም አልረሳቸውም። አንደኛው እንደ ሁለተኛ ቤቴ የምቆጥረው የአሸነፍ እንግዳ (ነፍሱን በአጸደ ገነት ያኑርልን) ቤት የተከሰተ ነው። አንድ ቀን ከወንድሜ ከማልለየው አበበ አሸነፍ ጋር ወደ እነሱ ቤት እንሄዳለን። እትሸት (የአበበ እናት) አልነበረችም። እንደለመድነው ከሞሰብ እንጀራ ከድስት ደግሞ ወጥ አድርገን በልተን ወጣን። ኋላ ላይ ስንሰማ ወጡ በቋንጣ ነበር የተሠራው።

ሁለተኛው ደግሞ አባቴ ‹‹ቀለም አምጣ›› ብሎ ወደ እነ ገነት ፀጋየ ቤት ላከኝ። እናቴ ‹‹ማርየ እንጀራ ብላ ካሉህ፤ በልቻለሁ በላቸው። ፋሲካ ስለሆነ ንክኪ አይጠፋውም›› አለችኝ። እኔም ‹እሽ› አልኩ። ልብ በሉ! ወደ ጎረቤት ቤት ከሄድክ ማንም ሁን ማን ቤት ያፈራውን ትበላለህ ማለት ነው። እዚያ ቤት ስሄድ ምግብ ብላ እንደሚሉኝ እናቴ ታውቃለች። በርግጥ እኔም ይሄ አይጠፋኝም።
እቤት እንደደረስኩ ‹ቀለም አልቋል› አልኩ። ‹‹እሽ እንሰጥሃለን፤ ግን እህል ቅመስ›› ተባልኩ። ‹ኧረ በልቻለሁ!› ብየ ድርቅ አልኩ። ‹‹የማይሆነውን!›› ሲሉኝ እሽ አልኩ። የሚያምር እንጀራ በሽንብራ ክክ ወጥ መብላት ጀመርኩ። መሀል ላይ ግን እናቴ ያለችው ነገር ደረሰ። ለካ ወጡ ስጋ ጣል ጣል ተደርጎበት ኖሮ ጥርሴን ያዝ አደረገኝ። እኔም ምንም እንዳልተፈጠረ ጠግቢያለሁ ብየ ሄድኩ። ይህ የሚሆነው ወጡን ሌላ ሰው ይሠራውና የሚያቀርበው ደግሞ ሌላ ይሆናል። በሆነው ነገር ቅር አይልህም። ለምን ቢባል ውስጡ ፍቅር፣ መውደድ፣ መተሳሰብ አለውና።

የአበባ አማረን ቤት ግን እንደ እራሴ ቤት ነው የምቆጥረው። እርሷም ከልጇ መኮነን ዘውዱ ለይታ አታየኝም። በነገራችን ላይ አበባ አማረ የገነት ፀጋየ አማረ አክስት ነች። ቤቷ ቤቴ እርሷም እንደ እናቴ ስል ውሎ ማደሪያየ መሆኑን መገመት አያዳግታችሁም። መኮነን ዘውዱ እና አበበ አሸነፍ ምስክርነት እንደምትሰጡ አልጠራጠርም። የጥር ጊዮርጊስ፣ ጥምቀት፣ ቡሄ፣ ጳጉሜን፣ አዲስ ዓመት እና መስቀል ሲመጡ ደስታችን ወደር የለውም። እና እንዲህ ብሎ ያደገን ሙስሊም ‹ኦርቶዶክስ ይጠላሀል!› ብትለው እንዴት ያምናል? ያውም ‹ሙስሊም ስለሆንክ ነው የሚጠላህ› ሲልህ ደግሞ ግራ ይገባሀል። ይህ የእኔ አስተዳደግ የብዙኃኑን ማኅበራዊ መስተጋብር ነፀብራቅ ነው።

ታዲያ ይህንን ማኅበረሰብ በሃይማኖት ምክንያት መለያዬት ይቻላል? አበበ እና መኮነን የእኔን መስገጃ ያቃጥላሉ? ይህ ሊሆን ይቅርና ሊታሰብ እንኳ አይችልም! ‹‹ታዲያ አሁን እየሆነ ያለው ምንድነው? ለምን ነው? በማን ነው?›› ካላችሁኝ መልሴ አላውቅም ነው። ይህንን ከስሩ መርምሮ በአጥፊዎቹ ላይ እርምጃ መውሰድ የመንግሥት ኃላፊነት ነው። ውድ የልጅነት ጓደኞቼ! የተለወጠ ነገር የለም በሉኝ?! ለዛሬ አበቃሁ።

ከማርዬ በለጠ የፌስቡክ ገጽ የተወሰደ

Previous articleለአምስት ዓመት ተብሎ የተቀመጠው መጠለያ ለ12 ዓመታት በመቆየቱ በቅርሱ ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
Next article“በሀገሪቱ መፍትሔ የሚመጣው የተንኮል ምንጩ ሲደርቅ ነው።” የባሕር ዳር ዪኒቨርሲቲ ተማሪዎች