“የአዕምሮ ውስንነት ያለባቸው ልጆችን ችግር ለመቅረፍ እንሠራለን” የአማራ ክልል የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ማኅበር አባላት

58

ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ማኅበር ምስረታ እና የማስተዋወቂያ ፕሮግራም በባሕር ዳር ተካሂዷል።
የማኅበሩ መመሥረት ችግራቸውን እንደሚቀርፍላቸው ወላጆች ተናግረዋል።

ወይዘሮ ዓለም የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባት ልጅ አለቻቸው። ልጃቸውን እንደሌሎች ልጆች ለማስተማር በማሰባቸው ትዳራቸው ፈተና ላይ ወድቆ ነበር። የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ልጆች የሚያስተምር ትምህርት ቤት አለመኖር ለወይዘሮ ዓለም ሌላው ፈተና ነበር።

ወይዘሮ ዓለም የልጃቸው ችግር በወሊድ ወቅት በተፈጠረ የሕክምና ስህተት የተፈጠረ እንጂ እርግማን አለመኾኑን ጠንቅቀው ያውቃሉ።

ወይዘሮ ዓለም ልጃቸውን በእድሜዋ ትምህርት ቤት አስገብተዋታል። በሚንቀሳቀሱበት ማንኛውም ቦታ ይዘዋት ይሄዳሉ። በዚህም ደስተኛ ናቸው። ሰዎች የሚያሳዮአቸው ፊት ልጃቸውን እንደሚረብሽ እና መደረግ እንደሌለበትም ያነሳሉ።

ለዚህ ችግር ተጋላጭ የኾኑ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ልጆችን ከመደበቅ ይልቅ አውጥተው ትምህርት ቤት እንዲውሉ፣ ከአቻዎቻቸው ጋር እንዲጫወቱ መፍቀድ አለባቸው ይላሉ።

የአዕምሮ እድገት ውስንነት በማንኛውም ሕፃን ላይ ሊከሠት የሚችል ችግር እንደኾነ የተረዱት ወይዘሮ ዓለም ለልጃቸው ልዩ እንክብካቤ እንደሚያደርጉ ነግረውናል።

የአማራ ክልል ሴቶች እና ሕፃናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዝና ጌታቸው አካል ጉዳተኞች በኢትዮጵያ ከ17 በመቶ በላይ እንደሚሸፍኑ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ አምስት አይነት አካል ጉዳተኝነት አለ፤ ከዚህ ውስጥ አራቱ ማኅበር የመሠረቱ ሲኾን የአዕምሮ እድገት ውስንነት ግን ከስድስት ወር በፊት መመሥረቱን ተናግረዋል።

ዘግይቶ የተመሠረተበትን ምክንያት ሲያስረዱም ልጆች በራሳቸው አቅም መንቀሳቀስ አለመቻል እና የወላጆች ድጋፍ በማስፈለጉ ነው ብለዋል።

ሌላው የመንግሥት እና የባለድርሻ አካላት ድጋፍ አናሳ መኾን ማኅበሩ ሳይመሠረት እንዲቆይ ምክንያት መኾናቸውን ተናግረዋል።

የማኅበረሰቡ ግንዛቤ አናሳ መኾን ልጆች ቤት ውስጥ እንዲደበቁ እና ቁጥራቸው እንኳን በትክክል እንዳይታወቅ ማድረጉን ገልጸዋል።

የማኅበሩ መመሥረት በቤት ውስጥ የተደበቁ ልጆች ወጥተው ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር እንዲቀላቀሉ ያስችላል ነው ያሉት።

መንግሥት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች መሠረት አድርገው ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ትምህርት ቤቶች እነዚህን ሕፃናት ሊያስተናግዱ የሚችሉ ክፍሎችን ቢያዘጋጁ፣ ወላጆችም መርገም ነው ከሚለው የተሳሳተ አመለካከት ወጥተው ልጆቻቸውን ከእድሜ አቻዎቻቸው ጋር እንዲውሉ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የአዕምሮ እድገት ውስንነት ማኅበር ሰብሳቢ ጳውሎስ ዘለቀ ከሴንትረም ኢንተርናሽናል ዘ ኔዘርላንድስ እና ቸሻየር ፋውንዴሽን ፎር ኢንክሉዥ በመተባበር መመሥረቱን ይናገራሉ።

አቶ ጳውሎስ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ልጆች ማሳደግ ትልቅ መሠጠትን ይጠይቃል ብለዋል።

ችግሩ ያለባቸው ልጆች እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ትምህርት ቤት የመግባት መብት ቢኖራቸውም ለሕፃናቱ የተሠጠው ትኩረት አናሳ በመኾኑ ማስተማር አለመቻሉን እና ትምህርት ቤት ቢገቡ እንኳን ሁሉንም በአንድ ክፍል አጭቆ የማስተማር ሂደት መኖሩን ጠቁመዋል።

ማኅበሩ የልጆች ፍላጎት እንዲሟላ አንደበት ኾኖ መሥራት አለበት የሚሉት አቶ ጳውሎስ የትምህርት እና የሥልጠና ፍላጎታቸው እንዲሟላ በርትተው እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

ሌሎች የኅብረተሠብ ክፍሎችም ችግሩን ተረድተው የማገዝ፣ ችግሩን ለሌሎች የማስረዳት ኀላፊነታቸውን በአግባቡ የመወጣት ኀላፊነት አለባቸው ብለዋል።

የማስተዋወቅ ፕሮግራሙ በአማራ ክልል ሴቶች እና ሕፃናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ በአማራ ክልል አዕምሮ እድገት ውስንነት ማኅበር፣ ከሴንትረም ኢንተርናሽናል ዘ ኔዘርላንድስ እና ቸሻየር ፋውንዴሽን ፎር ኢንክሉዥን ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።

ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል ሥራ ላይ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ፡፡
Next article“ለተመራቂዎች በሙሉ ፍሬያማ ህይወት እንዲገጥማችሁ እመኛለሁ” አቶ ደመቀ መኮንን