
ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ ሰለሞን ጣሰው በክልሉ ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሥራ አስፈጻሚው እንዳሉት በክልሉ የኃይል አገልግሎት ፍላጎት እያደገ መጥቷል።
በፍላጎቱ ልክ አገልግሎቱን መስጠት ባይቻልም ሰፊ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ኃይል እንዲያገኙም በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በጦርነቱ ምክንያት የወደሙትን የኤሌክትሪክ አገልግሎት መሰረተ ልማቶችን ለመጠገንም የግብዓትና የምንዛሬ ችግር ፈተና ኾኗል ነው ያሉት።
በዚህ ምክንያት አዲስ ኃይል ለሚጠይቁና መልሶ ግንባታ ለሚፈልጉም በቂ ሥራ መስራት አልተቻለም ብለዋል።
በአማራ ክልል የሚፈጠረው የኃይል መቆራረጥ ችግር 41 ነጥብ 4 በመቶ ከወሰን ማስከበርና ከመሰረተልማት ችግር ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል ሥራ አስፈጻሚው።
ችግሮችን ለመፍታት ሕግን የማስከበር፣ ብልሹ አሠራርን የመታገል፣ የተጀመሩ የሰብስቴሽን ግንባታዎች በወቅቱ እንዲጠናቀቁ ማድረግ ለችግሩ መፍትሔ ናቸው ብለዋል።
ለመፍትሔው ኅብረተሰቡ ተባባሪ እንዲኾንም ጥሪ አቅርበዋል።
ከ16 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የሚያካልለው የኃይል አገልግሎት በኅብረተሰቡ መጠበቅ አለበት ነው ያሉት።
የአገልግሎት ተደራሽነት ችግር በሌላ በኩል የመሰረተልማት ዝርፊያ አሳሳቢ ኾኗልም ብለዋል።
ችግርን የሚያራዝሙ ጉዳዮች በትኩረት በትብብር መፈታት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የትምምህርት፣ የጤና እና የውኃ ተቋማት ላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ችግር እንዳይኾን በትኩረት እየተሠራ እንደሆነም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!