
ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ሥልጠና 810 ሥራ ፈላጊዎች በሁለት ዙር የሕይወት ክህሎት የሥራ ላይ ሥልጠና እየወሰዱ መኾኑን የኮምቦልቻ ከተማ ሥራና ሥልጠና መምሪያ ገልጿል።
የኮምቦልቻ ከተማ ሥራና ሥልጠና መምሪያ የ2015 በጀት ዓመት ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ሥልጠና አተገባበርና አፈጻጸምን እየገመገመ ነው።
በግምገማ መድረኩ የፌዴራል ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተወካይ እና የከተማዋ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ ሥራና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ አይትባረክ ጌታሁን “ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ሥልጠና” ሦስት አላማዎች እንዳሉት ተናግረዋል።
ወጣቶችን በአመለካከትና በክህሎት ብቁ ማድረግ፣ በመንግሥትና በግል አሠሪ ተቋማት መካከል ፈጣንና ቀልጣፋ ግንኙነት መፍጠር፣ የሥራ ላይ ሥልጠናን ባሕል ማድረግ የሥልጠናው አላማዎች ናቸው።
በከተማዋ በ”ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ሥልጠና” በ2015 በጀት ዓመት 810 ሥራ ፈላጊዎች በሁለት ዙር የሕይወት ክህሎት የሥራ ላይ ስልጠና በመውሰድ ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከሠልጣኞቹ ውስጥ 405 ትስስር ተፈጥሮ የሥራ ላይ ልምምድ በማድረግ ላይ መኾናቸውንም ነው የተናገሩት።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሀገር ውስጥ ሥራ ስምሪት ማስተባበሪያ ዴስክ ኀላፊ ንዋይ አልታየ በሀገር አቀፍ ደረጃ በ”ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ሥልጠና” ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ ለ3 ዓመት የሚተገበር ፕሮጀክት መኾኑን አስረድተዋል፡፡
አቶ ንዋይ በሀገር አቀፍ ደረጃ 70ሺህ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል፡፡
በ2015 በጀት ዓመትም በ10 ከተሞች ከ15ሺህ በላይ ወጣቶች በ”ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ሥልጠና” እየተሳተፉ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
ሥራ ፈላጊዎቹ ሥልጠናውን ሲያጠናቅቁ የሥራ እድል ፈጠራ ትስስር ተጠቃሚ ይኾናሉ ነው ያሉት።
ፕሮጀክቱ በአማራ ክልል በሦስት ከተሞች በኮምቦልቻ፣ በባሕር ዳርና ጎንደር እየተተገበረ ይገኛል።
የሥልጠናው ተጠቃሚ ወጣቶች ከሥልጠናው ጠቃሚ ዕውቀት እያገኙ እንደኾነ ለአሚኮ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ከድር አሊ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!