
ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ወልቃይት ወረዳ ወፍ አርግፍ ከተማ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋም ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ኾኗል፡፡
ወረዳው በርካታ የመሠረተ ልማት ፍላጎቶች እና ክፍተቶች ቢኖሩበትም በጀት ስላልተመደበለት በውስጥ ገቢ እና በማኀበረሰብ ተሳትፎ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ክፍተቶችን ለይቶ እየሠራ መኾኑን አስታውቋል፡፡
ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ አካባቢውን በኃይል ይዞ በጭቆና ሲገዛ የነበረው ህወሃት እስከ ዛሬ ድረስ ለምን አገልግሎት ሰጪ ተቋም መገንባት ተሳነው የሚለው ጥያቄ ሌላ የሚያመላክተው አንድ ጠንካራ ሃቅ አለ፡፡ ወልቃይት የህወሃት የኪራይ ቤት እስክትመስል ድረስ በሩብ ምዕት ዓመት ቆይታው አንድ የመንግሥት አገልግሎት ሰጭ ተቋም አለመገንባቱ ከተከዜ ወዲህ ማዶ የነበራቸውን ግፍና ጭቆና በግልጽ አጉልቶ ያመላክታል፡፡
ህወሐት አካባቢውን በኃይል ከወረረበት ጊዜ ጀምሮ በአካባቢው ተወላጆች ላይ ከሚያደርሰው ሰብዓዊ ግፍ እና በደል በተጨማሪ መጠነ ሰፊ ምዝብራ ፈጽሟል የሚሉት የወልቃይት ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ክብረአብ ስማቸው ዓላማው የአካባቢውን ተወላጆች እና ባለርስቶች አፈናቅሎ ታላቋን ትግራይ መመስረት ነበር ይላሉ፡፡ ለዚህ ማሳያው በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ውስጥ አርሶአደሮችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ኢንቨስትመንት ቢያስፋፉም ከዘረፋና ምዝበራ ውጪ በአካባቢው ምንም አይነት መዋዕለ ንዋይ አለማፍሰሱ ነበር ይላሉ፡፡
ህወሃት በአካባቢው በቆየበት ያለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ወልቃይት ውስጥ ምንም አይነት የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋም አልገነባም የሚሉት አቶ ክብረአብ ወልቃይት ወረዳ ብቻ ለመንግሥት ተቋማት አገልግሎት መስጫ ቢሮ በየወሩ እስከ 300 ሺህ ብር ኪራይ ይከፍል ነበር ብለዋል፡፡
ወልቃይት እና አካባቢው በኃይል ወደ ቀደመ ማንነቱ ከተመለሰበት ጊዜ አንስቶም የወረዳ አሥተዳደሩ በኪራይ ሕንጻ መቆየቱን ያወሱት ዋና አሥተዳዳሪው ዞኑም ኾነ ወረዳው እስካሁን ድረስ በጀት ስላልተመደበለት ለአከራይ ባለሃብቶቹ ኪራይ መክፈል አልቻለም ብለዋል፡፡ ከባለሃብቶቹ ጋር በጀት ሲለቀቅ ኪራዩን ለመክፈል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን በማስታወስ፡፡
በየዓመቱ ሊከፈል የሚችለው የኪራይ ወጪ ተጠራቅሞ በወረዳው ውስጥ በርካታ የመሠረተ ልማት ክፍተቶችን ይሞላል ያሉት አቶ ክብረአብ ለዚህ ሲባል ከወረዳው የውስጥ ገቢ፣ ከአካባቢው ተወላጆች እና ከማኀበረሰቡ በተሰበሰበ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ ጅምር የሕንጻ ግንባታን አጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ አድርጓል ብለዋል፡፡ የአገልግሎት መስጫ ሕንጻ ግንባታው በወረዳው ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማኀበራዊ እና ፖለቲካዊ ተደራሽነትን ለማስፋት ያግዛል ብለዋል፡፡
ትናንት የወልቃይት እና አካባቢው ማኀበረሰብ መሠረታዊ ጥያቄ ከወያኔ ጭቆና እና አገዛዝ መላቀቅ ነበር ያሉት አቶ ክብረአብ ነጻነቱን በወገኖቹ እና ልጆቹ የጋራ ትብብር ባረጋገጠ ማግስት ወደ መሠረታዊ አገልግሎት ተሸጋግሯል ብለዋል፡፡ ዛሬ ላይ “ወልቃይት ከነጻነት ወደ ልማት ተሸጋግሯል” ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው የአካባቢውን ማኀበረሰብ የዘመናት ጭቆናውን እና በደሉን የሚመጥን ፍትሕ ይጠብቃል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!