
ባሕር ዳር: ሐምሌ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሽግግር ፍትሕን አስመልክቶ ለአውሮፓ ኅብረትና አባል ሀገራት ተወካዮች በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማብራሪያ ተደርጓል፡፡
ማብራሪያውን የሰጡት የፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) እና የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የፖለቲካ አማካሪ አምባሳደር ሚኒልክ አለሙ ናቸው።
በገለፃው ላይ በዋናነት የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮች እና አባል ሀገራት ተወካዮች ተገኝተዋል።
የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን (ዶ/ር) በሽግግር የፍትህ ፖሊሲ አማራጮች አፈፃፀም እና የተከናወኑ ተግባራት ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡
የሽግግር ፍትህ የፖሊሲ አማራጮች የሥራ ቡድን አደረጃጀትን በሚመለከት፣ በቡድኑ የተቀረፀውን የሽግግር ፍትህ የፖሊሲ አማራጮችን እና በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እስካሁን ከባለድርሻ አካላትና ከአጋር አካላት ድጋፍ ጋር የተካሄደውን ልዩ ልዩ ሕዝባዊ ምክክርን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የቀጣይ የአፈጻጸም ዕቅዶች በተመለከተም ገለጻ ማድረጋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!