
ባሕር ዳር: ሐምሌ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የምክር ቤት አባላቱ ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ያቀረቡትን የክልሉ አስፈጻሚ አካላት እቅድ አፈጻጸም የተጠቃለለ ሪፖርት መነሻ በማድረግ የልማትና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን እያቀረቡ ነው።
በምክር ቤት አባላቱ ከተነሱት ጥያቄና አስተያየቶች መካከልም:-
✍️በምሥራቅ ጎጃም ዞን የዞንና የወረዳ ይከፈልልን የሕዝብ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እያገኙ አይደለም። ጥያቄዎቹ ተገቢውና አፋጥኝ ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል።
✍️ በክልሉ የሰላም ጉዳይ ፈታኝ ኾኗል።
የሰላም ማስፈን፣የሕግ የበላይነትንና የሕዝብ ደኀንነትን ማረጋገጥ ጉዳይ በልኩ ሊሠራበት ይገባል።
በክልሉ አማራን የማይመጥን የመገዳደል ድርጊቶች እየታዩ ነው። የሰላም እጦቱ ምክንያት ተጢኖ በውይይት ሊፈታ ይገባል።
✍️ምክር ቤቱ በክልሉ ለተፈጠረው የሰላም እጦት አቅጣጫዎቹን ማስቀመጥ አለበት። የክልሉ መንግስት ፣ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሁም ሕዝቡ በጋራ መወያየት አለበት።
✍️አኮረፍን ከሚሉ ወንድሞቻችን ጋር በጋራ ቁጭ ተብሎ መወያየት ያስፈልጋል። ሰፊ ውይይትና ንግግሮች መደረግ አለባቸው ፣ አማራ የራሱን ችግር በራሱ መፍታት አለበት።
✍️መላ ሕዝብን በማነጋገር ለሰላም ዘብ መኾን እንዲችል ማድረግም ይገባል። የትጥቅ ትግልን ያነገቡ አካላት ለክልሉ ሕዝብ ኅልውና አደጋ መኾን የለባቸውም።
✍️የክልሉ መንግስት የአማራ የዘመናት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የሚያደርጋቸው ሙከራዎች እንዳሉ ኾነው ጠንከር ያለ የሕዝብን መብትና ጥቅም የማስከበር ኀላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል።
✍️ሕዝብ በመንግስት ላይ፣ ሕዝብ በሕግ የበላይነት ላይ አመኔታው እንዳይቀንስ ጠንከር ያሉ፣ የተጠኑ ውይይቶችና ስምምነቶች መደረግ አለባቸው። ችግሮቻችንን የምንፈታበት መንገድ ጉዳዩንና ዘመኑን በሚዋጅ መልኩ መኾን አለበት።
✍️የግብርና የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት አሁንም ከችግሩ አልተሻገረም። ቅንጅታዊ አሠራር እና ቁርጠኝነት ይፈልጋል።
✍️የኑሮ ውድነት ከዚህም በላይ ጫናው እንዳይበረታ አምራችነት ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል።
በተለመደው የግብርና ዘይቤ የኑሮ ውድነቱን መቋቋም አይቻልም። ልምድ ያላቸው የግብርና ሥራዎች መቀመርና በስፋት መተግበር አለባቸው።
✍️የአገልጋይነት ስሜት ጠፍቷል።
የመንግስት ሠራተኛው የተቀጠረበትን ሙያ እያጎደለ፣ ተጨማሪ ገቢ የሚያገኝበት ሥራን እያማተረ ነው፣ ምክንያቱ ደግሞ ዝቅተኛ ደሞዝተኝነት የፈጠረው ነውና ሊታሰብብት ይገባል።
✍️ የኢንቨስትመንት መዳረሻ የኾኑ አካባቢዎች በኃይል አቅርቦት ምክንያት በሚገባቸው ልክ እንዳይሠሩ አድርጓል ፣ኃይል አቅርቦት ላይ ተገቢው አሠራር መኖር አለበት። የሚሉና ሌሎችም ሀሳቦች እየተነሱ ነው።
ዘጋቢ :-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!