“የወይራ ዛፍ ሞኝ የለውም” ጠገዴዎች

63

ሁመራ: ሐምሌ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ነዋሪዎቹ ዛሬ ላይ ኾነው ስለትናንቱ ማንነታችው ሲናገሩ በንግግሮቻቸው መካከል ሁሉ ቀኝ አዝማች እና ግራዝማች፤ ፊት አውራሪ እና ቢትወደድ የሚሉ የማዕረግ ሥሞች ይበዛሉ፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ የዘመናት የነጻነት ተጋድሎ፣ የጎንደር ሥርወ-መንግሥት ታሪክ እና የበጌምድር ማንነት ደብዛው እንዲጠፋ ከሩብ ምዕት ዓመት በላይ አማራ ጠል ትርክት ተሰብኮበት እንኳን አሁንም ድረስ የአማራነት ለዛው ከአካባቢው ፈጽሞ አልጠፋም፡፡ ጠገዴ አሁንም ድረስ በ “ፀ” ሳይኾን “ጠ” ላይ እንደጸና ነው፡፡

ከአንገረብ ምላሽ እስከ ካዛ ወንዝ ድረስ ቆላ ከደጋ የሚሸፍነው የጠገዴ ምድር ጀግና ማብቀል ያውቅበታል ይሉታል የሀገሬው ሰዎች፡፡ ነዋሪዎቹ “ሀገር በለው ጠገዴ” እያሉ ስላለፈው ታሪካቸው ሲናገሩ ግራዝማች ዘርተው ቀኝ አዝማች የሚያበቅሉ፣ ፊት አውራሪ አጭተው ቢትወደድ የሚድሩ፣ ባላምባራስ ተቀብለው ልጅ የሚሾሙ ይመስላሉ፡፡ የታሪካቸው ደርዝ፣ የማንነታቸው ወዝ እና የድንበራቸው ጠርዝ ጎንደሬ ስለመኾናቸው እማኝ አይሻም፡፡

የቀደመ ታሪካቸውን ከአብርሃም ቶራ የሚመዝዙት ጠገዴዎች የወረዳ መናገሻቸው ጥንታዊቷ የቅራቅር ከተማ እንደነበረችም ይናገራሉ፡፡ ከሀገሪቷ መዲና አዲስ አበባ የቀደመ የከተሜነት ታሪክ እንደነበራት የሚነገርላት ቅራቅር የጠገዴ ምድር ማዕከል ተደርጋ ትወሰዳለች፡፡ ከምድረ ገበታ እስከ ጋሞ ቤተ ማርያም፣ ከደባስ ክንድሽ እስከ አዴትና ቶራት፣ ከዳራ ደቅአባ እስከ ጨኳርኩዶ፣ ከደብረ ሐርያ እስከ ሻግኔ ድረስ የሚካለለው የጠገዴ ታችኛው ምድር ክፍለ ሀገሩ በጌምድር፣ አውራጃው ደግሞ ወገራ እንደነበር ታሪክ ጠቅሰው መረጃ ነቅሰው ከልጅ እስከ አዋቂ ዛሬም ድረስ ይናገራሉ፡፡

በሰንሰለታማ ተራሮች ከሁለት የተከፈለው የጠገዴ ምድር ከባሕር ጠለል በላይ እስከ 3 ሺህ ሜትር ከፍታ ያለው ደጋማው ክፍል የቀደሙት ባላባቶች መኖሪያ እንደነበር ይነገራል፡፡ ከባሕር ጠለል በላይ እስከ 500 ሜትር የሚደርሰው ቆላማው ክፍል ደግሞ ደጋው ላይ የሚኖሩት ባላባቶች በቅራትነት የሚያርሱት እና ከብት የሚያረቡበት ትርፍ አምራች አካባቢ ነው፡፡ ከዳንሻ እስከ ግጨው፣ ከወይንናት እስከ ሎሚወንዝ፣ ከማይደሌ እስከ ጎቤ፣ ከእንጣቢላ እስከ ትፋሻ፣ ከቅራቅር እስከ ማክሰኞ ገበያ ከአንድ ማሳ እሸት ፣ ከአንድ ላም ወተት የሚጋሩ የጠገዴ ምድር ወንድማማቾች ናቸው፡፡

ከእምነት እስከ ማንነት፣ ከባሕል እስከ ትውፊት እና ከታሪክ እስከ መልካ ምድር ለዘመናት አንድ የነበረው ጠገዴ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ከሁለት ተከፍሎ ይለያይ ዘንድ ተገደደ፡፡ የትምህርት ቤት ድንበር እና የከተማ ሠፈር የለያቸው ወንድምአማቾች “ታላቅ እና ታናሽ መለያየታችን ለሰሚውም ግራ ነው” ቢሉም ጩኸታቸውን ሰሚ ጠፋ፡፡ ይባስ ብሎ አማራ ነን ያሉ ጠገዴዎች ታሰሩ፣ ተሰወሩ፣ ተደበደቡ አንዳንዶቹም ከሰብዓዊነት በራቀ መልኩ ወደ ገደል ተወረወሩ፡፡

የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ያ ሁሉ መከራ እና ስቃይ እየወረደባቸውም ግን ጎንደሬነታቸውንም፣ አማራነታቸውንም በግልጽም ፣ በህቡዕም ሲናገሩ እና ሲዘምሩ ቆይተዋል፡፡ “አርባው ሲደርስ” እና የግፍ ጽዋው ሞልቶ ሲፈስስ ወደ ናፈቅነው ማንነታችን ተመልሰናል የሚሉት የጠገዴ አማራዎች በቋንቋቸው ሲቀኙ “የወይራ ዛፍ ሞኝ የለውም” ይላሉ፡፡ ጩኸታችንም፣ ሞታችንም፣ ስደታችንም የማታ ማታ ፍሬ አፍርቷል ማለታቸው ነው፡፡ በጥረታችን ያልተሳካ ህልም እና በተገኘው ድል ያልታከመ ህመም የለንም ይላሉ በኩራት፡፡

በጠገዴ ወረዳ ምድረ ገበታ ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ የኾኑት እና የ66 ዓመት የእድሜ ባለጸጋው አቶ ተመስገን ዘውዱ ጠገዴ ታሪኩ፣ ማንነቱ፣ እትብቱ እና እምነቱ ሁሉ በጌምድሬ ስለመኾኑ ታሪክ ምስክር ነው ይላሉ፡፡ በጎንደር ጠቅላይ ግዛት በዳባት አውራጃ ቢትወደድ አዳነ መኮንን አካባቢውን ሹም ኾነው ሲመሩ ልጅ ኾኘ አውቅ ነበር የሚሉት አቶ ተመስገን ከደስታ እስከ ሃዘን፣ ከባሕል እስከ ማንነት፣ ከእሴት እስከ እርስት ጠገዴ መገለጫው አማራነት ነበር ይላሉ፡፡ ምንም እንኳን ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ገደማ ጠገዴ ከርስቱ እና ከማንነቱ ተከፍሎ የመከራ ዘመናትን ቢያሳልፍም “የወይራ ዛፍ ሞኝ የለውም” እንዲሉ ሁሉንም የማንነቱን መገለጫዎች ሳይዘነጋ ቀን እየጠበቀ እስከ ነጻነት አጥቢያ ዘልቋል ይላሉ፡፡

የጠገዴ አውራዎች፣ ነጭ ለባሾች እና ታላላቅ ሰዎች በወያኔ ዱካቸው እየተፈለገ ታድነው ጠፍተዋል ያሉን ደግሞ በጠገዴ ወረዳ ጨኳር ኩዶ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት አቶ ጌታሁን በላይ ናቸው፡፡ ህውሐት ከሁሉም አካባቢዎች ዘግይታ የያዘችው አካባቢ ጠገዴ ነው የሚሉን ነዋሪዎቹ አጋር ታጥቶ እና መደራጀት ጠፍቶ እንጂ ከመጀመሪያውም የጠገዴን ወደ ትግራይ መካለል አሜን ያለ አልነበረም ነው ያሉን፡፡ በዱር በገደሉ፤ በዋሻ ሽንተረሩ ለማንነታቸው እና ለነጻነታቸው በርካቶች ከወያኔ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው ማለፋቸውን በማንሳት፡፡

ባለፈው ዘመን ከጠፋው ህይዎት እና ከተዘረፈው ሃብት በላይ በማንነት መገለጫዎቻችን ላይ የተቃጣው ጥቃት ታሪክ ይቅር የሚለው አይደለም የሚሉት አቶ ጌታሁን በቋንቋችን እንዳንገለገል፣ ስለማንነታችን እንዳንታገል፤ በጥበባችን እንዳናጌጥ ፣ በወንድነታችን እንዳናመልጥ እግር ከወርች ተቀፍድደን ቆይተናል ይላሉ፡፡ ወያኔ ወልቃይት ጠገዴን፣ ጠለምትን እና ራያን በጭቆና ደፍጥጦ ከገዛበት ኃይሉ ይልቅ የእኛ ቸልታ እና የወንድሞቻችን ዝምታ ያስገርማል ሲሉ የትናንቱን ግፍ ከዛሬው ነጻነት ጋር ያንሰላስሉታል፡፡

አስተያየት ሰጭዎቹ “ሞኝ ከቤቱ ፣ ብልህ ከጎረቤቱ ይማራልና” ቢያንስ መደራጀት ኃይል መኾኑን ከጎረቤቶቻችን መማር ይኖርብናል ይላሉ፡፡ ያለፈው ጭቆና፣ ግፍ እና በደል በልጅ ልጆቻችን እንዲደገም አንፈልግም የሚሉት ጠገዴዎች በኃይል የተገኘውን ነጻነት ከማጣጣም ባለፈ ዘላቂ ለማድረግ መረባረብ ለነገ አይባልም ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያለውን እህትማማችነት እና ወንድማማችነት የበለጠ ለማጎልበት አጠናክረን እንቀጥላለን” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)
Next articleየአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት የክልሉን ሰላም ለማስፈን በውይይትና በንግግር ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተናገሩ።