የብሔረ ብጹዓን አፄ መልክዓ ሥላሴ ገዳም መነኮሳት ወደ ገዳማቸው እየተመለሱ መሆናቸው ተገለጸ።

57

ባሕር ዳር: ሐምሌ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ኤልያስ ወረዳ የሚገኘው የብሔረ ብጹዓን አፄ መልክዓ ሥላሴ ገዳም መነኮሳት ወደ ገዳማቸው እየተመለሱ መሆናቸውን የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት
ገልጿል።

ባለፈው ጊዜ በገዳሙ በተከሰተው ከፍተኛ ችግር ምክንያት ከበዓታቸው ወጥተው የነበሩ አባቶችንና እናቶችን ወደ ቀደመ ቦታቸው እንዲመለሱና ገዳማዊ ሕይዎታቸውን እንዲቀጥሉ የማድረግ ሥራ በሀገረ ስብከቱና በሌሎችም አካላት ትብብር እየተሠራ መሆኑን ከሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ አብራርቷል።

ይህ የተገለጸው ዛሬ ወደ ገዳሙ ለመመለስ ፈቃደኛ ለሆኑ እናቶችና አባቶች በሀገረ ስብከቱ ግቢ ውስጥ በብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጸሎትና ቡራኬ ሽኝት በተደረገበት ወቅት ነው።

ገዳማውያኑ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጸሎትና ቡራኬ ከተቀበሉ በኋላ በሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊና በሀገረ ስብከቱ የገዳማት ክፍል ኀላፊ መሪነት ወደ ገዳማቸው እንዲጓዙ ተደርጓል።

ሌሎችንም አባቶችና እናቶች ወደ ገዳሙ የመመለስ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጸው ሀገረ ስብከቱ፤ በችግሩ ምክንያት ከገዳማቸው ተፈናቅለው በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ አባቶችና እናቶች እንደ ዛሬዎቹ ሁሉ ወደ ገዳማቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያለውን እህትማማችነት እና ወንድማማችነት የበለጠ ለማጎልበት አጠናክረን እንቀጥላለን” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)
Next article“ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያለውን እህትማማችነት እና ወንድማማችነት የበለጠ ለማጎልበት አጠናክረን እንቀጥላለን” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)