ለአምስት ዓመት ተብሎ የተቀመጠው መጠለያ ለ12 ዓመታት በመቆየቱ በቅርሱ ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

195

ለአምስት ዓመት ተብሎ የተቀመጠው መጠለያ ለ12 ዓመታት በመቆየቱ በቅርሱ ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የፌዴራል ቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለስልጣን በበኩሉ መጠለያውን ለማንሳት ጥናት እየተካሄደ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 13/2012ዓ.ም (አብመድ)ለላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ለቅረሱ ደኅንነት ተብሎ የተቀመጠው መጠለያ ከፀሐይ ባለፈ ከዝናብ እየተከላከለ እንዳልሆነ የላልይበላ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
ዲያቆን ፈንታ ታደሰ በላልይበላ ከተማ በአስጎብኝነት ነው የሚሠሩት፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ ለአምስት ዓመታት ተብሎ የተቀመጠው መጠለያ አገልግሎት መስጠት ከሚገባው ጊዜ በላይ በመቀመጡ በፀሐይና ዝናብ መፈራረቅ ምክንያት ብረቶቹ መዛጋቸውን አስጎብኙ አስረድተዋል፡፡ የመጠለያዎቹ ምሰሶዎች የቆሙበት ቦታ ጥልቀት የሌለበት እና በአርማታ ብቻ በመሆኑ ካላቸው ክብደት እና ከጊዜው እርዝማኔ ጋር ተዳምሮ በቅርሱ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውንም ነው ዲያቆን ፈንታ የገለጹት፡፡
የቤተ ማሪያም አገልጋይ እና የቅርስ ጥገና ባለሙያ ቄስ አሰግድ ደምሴ እንደገለጹት ደግሞ የመጠለያው ምሰሶ ያረፈበት ቦታ መሠረት የለውም፤ መጠለያውም ለረጅም ጊዜ ከማገልገሉ የተነሳ ዝናብ በማስገባቱ በቅርሱ ላይ ጉዳት እያደረስም ይገኛል፡፡ ‹‹መጠለያው የተቀመጠው ቅርሱ ጥገና እስኪደረግለት ለአምስት ዓመት በጊዜያዊነት ቢሆንም ጥገናው በመረሳቱ እንደ ቋሚ ቅርስነት እንዲታዩ አድርጓቸዋል፡፡ መጠለያውን ከተሸከሙት አራቱ ምሰሶዎች ውስጥ የአንዱ ቋሚ ክብደት 40 ኩንታል የሚመዝን ነው፤ ምሰሶዎቹ ካረፉበት በታች በሚገኙ ቅርሶች ላይ ጉዳት የማድረስ ዕድሉ ሰፊ ነው›› ብለዋል አስተያየት ሰጭው፡፡
የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላልይበላ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪ አባ ጽጌ መዝገቡ እንደተናገሩት ደግሞ ቅርሱን ከዝናብ እና ከፀሐይ ለመከላከል በ2000 ዓ.ም የተቀመጠው መጠለያ ለአምስ ዓመታት ተብሎ ቢሆንም 12 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የአብያተ ክርስቲያናቱ አስተዳዳሪ እንደገለጹት የመጠለያዎቹ መሰሶዎች ያረፉበት ቦታ በውስጡ ቤተ መቅደስ ያለበት የውስጥ ለውስጥ መንገድ አናት ላይ በመሆኑ ወደ ውስጥ የመደርመስ ዕድሉ የሰፋ ነው፡፡
አባ ጽጌ መዝገቡ እንዳሉት መጠለያዎቹ ሲሰሩ የነበረው የነፋስ ግፊት አሁን ካለው ከ50 በመቶ በላይ መጨመሩ በባለሙያዎች በመረጋገጡ የመጠለያው ምሰሶዎች የመነቃነቅ እና መውደቅ ዕድላቸው ሰፍቷል፤ ስለሆነም ለማስነሳት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የፌዴራል ቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረዳት ፕሮፌሰር) እንደተናገሩት የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በመጠለያዎቹ መነሳት ተስማምቷል፡፡ ይሁን እንጅ እንዴት እና በምን እንደሚነሳ ራሱን የቻለ ጥናት ስለሚያስፈልግ በፈረንሳይ መንግሥት በኩል ጥናት በመደረግ ላይ ይገኛል ብለዋል ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡፡ አጠቃላይ የቅርሱ ጥገና ጥናት በሚቀጥለው ዓመት ታኅሳስ የሚጠናቀቅ ቢሆንም ችግሩ በታየበት የቤተ አባ ሊባኖስ መጠለያ የጥገና ጥናቱ ከመጠናቀቁ በፊት እንደሚነሳ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገልጸውልናል፡፡
እንዲነሱ ጥያቄ እየቀረበባቸው ያሉት መጠለያዎቹ በቤተ ማሪያም፣ በቤተ መድኃኒያለም፣ በቤተ አማኑኤል እና በቤተ አባ ሊባኖስ ነው የተሠሩት፡፡ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ከሰሞኑ ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጋር በነበራቸው ቆይታ ከተነጋገሩባቸው ጉዳዮች አንዱ የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የጥገና ጉዳይ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ

Previous articleበኩር ጋዜጣ ታኀሳስ 13/2012 ዓ/ም ዕትም
Next articleትናንት ናፈቀኝ!